
ባሕር ዳር፡ ነሐሴ 29/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ከደቡብ ወሎ ዞን መቀመጫ ደሴ ከተማ 47 ኪሎ ሜትር፣ ከአልብኮ ከተማ ደግሞ 12 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ይገኛል።
260 ዓመታትን ያስቆጠረ እና በኢትዮጵያ የመጀመሪያው የመውሊድ በዓል የተከበረበት ታሪካዊ ቦታ እንደኾነም ይነገራል ጀማ ንጉሥ።
በ1756 ዓ.ም በሐጅ ሰዒድ ሙጃሂድ እንደተቆረቆረ ይነገራል። ሐጅ ሰይድ ሙጃሂድ በ1735 ዓ.ም በወረባቦ ነበር የተወለዱት። በ20 ዓመታቸው የሐጅን ሥነ ሥርዓት ለማከናወን ወደ መካ ተጓዙ፤ መካ ላይ አርፈው የሐጅ ሥነ ሥርዓት ካጠናቀቁ በኋላ ወደ ነቢዩ ሙሐመድ (ሰ.ዐ.ወ) መቃብር ቦታ መገኛ መዲና ከተማ አቀኑ።
መዲና ላይ ለወራት ቆይተው የሄዱበትን ጉዳይ እንዳጠናቀቁ ወደ ኢትዮጵያ ተመለሱ። ሀገራቸው ከገቡ በኋላም ጀማ ንጉሥ ሲደርሱ “የእኛ ቦታ ይቺ ናት” በማለት ጀማ ንጉሥን ማዕከላቸው አደረጉ።
ከዚያን ጊዜ ጀምሮ መውሊድ እና ሌሎች ሃይማኖታዊ ክዋኔዎች ወደ ተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች እንደተስፋፋ ይነገራል። መውሊድም ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ወደ ኢትዮጵያ በመስፋፋት እንዲከበር ተደረገ።
ሐጅ ሰዒድ ሙጃሂድ በቦታው መስጅዱን በመመሥረት በርካታ ምሁራንን አስተምረዋል፤ በርካታ ኪታቦችንም ጽፈዋል።
ከጻፏቸው ኪታቦች መካከል ካሸፈል ኩሩብ፣ ወሲለቱል አስና፣ ሂጀቱን ሷዲቂን፣ አዳቡል ኸልቅ፣ መኡነቱል አልፈቂርና ሪሳለቱል ኢህዋን ይጠቀሳሉ፡፡
ጀማ ንጉሥ በቃል ኪዳን የተመሠረተ መስጅድ በመኾኑ በእስልምና ሃይማኖት ተከታዮች ዘንድ የመውሊድ በዓል በድምቀት ከሚከበርባቸው ቦታዎች ዋነኛው አድርጎታል።
በዓሉ በተከታታይ ለሦስት ቀናት እንደሚከበርም ይነገራል።



በበዓሉ ላይ ሰዎች ሃይማኖት፣ ጾታ፣ ዕድሜ እና ሌሎች ቅድመ ኹኔታዎች ሳይገድባቸው በፍቅር እና በአንድነት በጋራ ያከብራሉ፡፡
ጀማ ንጉሥ በርካታ የሚዳሰሱ እና የማይዳሰሱ እንደ ልዩ ልዩ ኪታቦች፣ ድቤ፣ ረከቦት፣ ጀበናዎች፣ መካነ መቃብሮች እና ገድል የተፈጸመባቸው የወይራ እና የመሳሰሉ ዛፎችም መገኛ መኾኑን ከደቡብ ወሎ ዞን ባሕል እና ቱሪዝም መምሪያ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።
ዘጋቢ፦ ዳግማዊ ተሠራ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን