መውሊድ በዓለም ላይ

9
ባሕር ዳር: ነሐሴ 29/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ዛሬ ላይ ለ1 ሺህ 500ኛው የመውሊድ በዓል እየተከበረ ይገኛል። መውሊድ እንደ አንድ እስላማዊ በዓል መከበር የጀመረው በዘመነ ሒጅራ አቆጣጠር ከሦስተኛው መቶ ክፍለ ዘመን መጨረሻ ጀምሮ እንደነበር መረጃዎች ያሳያሉ፡፡
የመውሊድ በዓል መከበር የጀመረው በጥንታዊቷ ግብጽ እንደነበር ታሪክ ይናገራል የሚሉት የኢትዮጵያ እና ዓረቡ ዓለም የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነት ተመራማሪ ፕሮፌሰር አደም ካሚል ዘመኑም ሦስተኛው መቶ ክፍለ ዘመን መጨረሻዎቹ አካባቢዎች ጀምሮ እንደነበር ይገመታል ይላሉ፡፡
የመውሊድ በዓል አከባበር መሠረታዊ መነሻዎች ምንድን ናቸው የሚል ጥያቄ አሚኮ ያነሳላቸው ፕሮፌሰር አደም ሲመልሱ እስልምና በዓለም ላይ መስፋፋቱን ተከትሎ በርካታ አሳቢያንን እና ፈላስፎችን ባፈራችው ጥንታዊቷ ኢራቅ በወቅቱ ለነበረው የሀገሪቱ ንጉሥ አንድ የሕዝብ ቅሬታ ቀረበ ይላሉ፡፡
የሕዝቡ ቅሬታም በሀገራቸው ቁርዓንን የሚያስቀሩ እና የነብዩ ሙሐመድን (ሰ.ዐ.ወ) ሐዲስን የሚያስተምሩ በርካታ መሻኢኮች የመኖራቸውን ያክል ለምን ስለነብያችን የተጻፈም ኾነ የሚያስተምር ታጣ የሚል ነበር፡፡
የኋላ ኋላ እስልምና በአንዳንድ የአውሮፓ ሀገራት የገጠመው እንቅፋት እና መከራ ጥንታዊያኑ ኢራቃዊያን ቀድመው ያነሱት እስልምናን በአግባቡ ያለመረዳት ችግር ነው ተብሎም ይታመናል፡፡
የኾነ ኾኖ የሀገሪቱ ንጉሥ የሕዝቡን ቅሬታ እና አቤቱታ በበጎ ጎኑ ተመልክቶት ነበር የሚሉት ፕሮፌሰር አደም የነብዩን የሕይዎት ጉዞ፣ አስተምህሮ እና ማንነት በሚገባ ተደራጅቶ እንዲሰነድ እንዳደረገ ይነገራል ይላሉ፡፡
በዚህም ነብዩ ሙሐመድ (ሰ.ዐ.ወ) የተወለዱት፣ ከመካ ወደ መዲና የተሰደዱበት እና ያረፉበት ወር አሁን ያለንበት ረቢዑል አወል ነበር፡፡
እስልምናን በ615 ዓመተ ሒጅራ እንደተቀበለች የሚነገርላት ኢትዮጵያን ጨምሮ በርካታ ሀገራት የመውሊድን በዓል በደመቀ መልኩ ያከብራሉ የሚሉት ፕሮፌሰር አደም በተለይም በፈረንሳይ እና ስዊድን እስልምና የገጠመው ፈተና ሃይማኖታዊ አስተምህሮውን ካለመረዳት እና የነብዩን አበርክቶ ካለማወቅ የመነጨ በመኾኑ መውሊድ አንድ ሃይማኖታዊ በዓል ኾኖ መከበር እንዳለበት የሚስማሙት በርካቶች ናቸው ይላሉ፡፡
አሁን ላይ በበርካታ የዓለም ሀገራት ዘንድ መውሊድ እንደ አንድ ሃይማኖታዊ በዓላት በድምቀት ይከበራል ይላሉ፡፡
እስልምናን በመቀበል ከመዲና በ8 ዓመታት፣ ከኢራቅ በ18 ዓመታት፣ ከፈረንሳይ በ21 ዓመታት፣ ከግብጽ በ24 ዓመታት፣ ከሞሮኮ በ27 ዓመታት፣ ከሱዳን በ36 ዓመታት፣ ከቱርክ እና ኢራን በ76 ዓመታት እንዲሁም ከሕንድ እና ፓኪስታን በ170 ዓመታት የምትቀድመው ኢትዮጵያ መውሊድን እንደ አንድ ሃይማኖታዊ በዓል በአዋጅ ማክበር የጀመረችው በዘመነ ደርግ እንደነበር ፕሮፌሰር አደም ነግረውናል፡፡
ኢትዮጵያ መውሊድን በተለየ መልኩ ለማክበር ከሌሎች ሀገራት የበለጠ በርካታ ምክንያቶች አሏት የሚሉት ፕሮፌሰር አደም ኢትዮጵያዊያን በመላው ዓለም “ነብዩ ያከበሯቸው ሀገር ዜጎች” በሚል ይታወቃሉ ይላሉ፡፡ ይኽም ነብዩ ሙሐመድ (ሰ.ዐ.ወ) ለሐበሻ ምድር ያላቸውን ፍቅር እና ለሐበሾች ያላቸውን ክብር የሚገልጥ እንደኾነም ነግረውናል።
ዘጋቢ፦ ታዘብ አራጋው
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
Previous article“መውሊድ የሠላም እና የአብሮነት በዓል ነው” ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ
Next articleየኢፌዴሪ ፕሬዝዳንት ታዬ አጽቀሥላሴ የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት፦