
ጎንደር፡ ነሐሴ 28/2017 ዓ.ም (አሚኮ)
በማዕከላዊ ጎንደር ዞን ላይ አርማጭሆ ወረዳ
ተማሪዎችን ለመደበኛው የትምህርት ዘመን ለማዘጋጀት የክረምት ማጠናከሪያ ትምህርት ሲሰጥ መቆየቱን የወረዳው ትምህርት ጽሕፈት ቤት ገልጿል። ትምህርቱ እስካሁንም ድረስ እየተሠጠ ነው።
መምህራን የማጠናከሪያ ትምህርቱን በአግባቡ እየሰጡ መኾናቸውን በልማት በር አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ትምህርታቸውን ሲከታተሉ ያገኘናቸው ተማሪ ትዕግስት ማንደፍሮ እና ተማሪ ዘሚካኤል አስረሳዉ ተናግረዋል።
በሂደቱ ዕዉቀትን እየገበዩ መኾኑን ጠቅሰዋል።
የክረምት ማጠናከሪያ ትምህርት መማራቸው ለመደበኛው የትምህርት ዓመት ከፍተኛ እገዛ እንደሚያደርግላቸው ተማሪዎች አንስተዋል።
በልማት በር አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የክረምት ማጠናከሪያ ትምህርትን በበጎ ፈቃድ እየሠጡ ከሚገኙት መምህራን መካከል መምህር ጥላሁን አሰሜ አንዱ ሲኾኑ ተማሪዎችን ለማብቃት እየሠሩ መኾናቸውን ጠቅሰዋል። ለማጠናከሪያ ትምህርት የሚኾኑ ቁሳቁሶች መሟላታቸው ለመማር ማስተማር ተግባሩ አግዟል ብለዋል።
በክረምት ወራት ሰፊ ጊዜ ያለ በመኾኑ ለተማሪዎች በቂ ጊዜ ሰጥቶ ለማገዝ እንዳስቻለም ነው የጠቆሙት።
የላይ አርማጭሆ ወረዳ ትምህርት ጽሕፈት ቤት ኀላፊ መልሰው አዛናው የክረምት ማጠናከሪያ ትምህርቱ
በአምስት ትምህርት ቤቶች እየተሰጠ መኾኑን ተናግረዋል። በዚህም ከ500 በላይ ለሚኾኑ ተማሪዎች የማጠናከሪያ ትምህርቱ እየተሰጠ ነው ብለዋል።
የማጠናከሪያ ትምህርቱ በተገቢው መንገድ ተማሪዎችን እንዲያንጽ ለትምህርት ቤቶች የሚያስፈልጉ ቁሳቁሶች መሟላታቸውን ኀላፊው አንስተዋል።
በማዕከላዊ ጎንደር ዞን በክረምት ወራት የመማሪያ ክፍሎች ጥገና እና የማጠናከሪያ ትምህርት ሲሰጥ መቆየቱን የነገሩን ደግሞ በዞኑ ትምህርት መምሪያ የሥርዓተ ትምህርት ዝግጅት እና ትግበራ ቡድን መሪ ታከለ መንገሻ ናቸው። በዞኑ በ157 ትምህርት ቤቶችም ጥገና መካሄዱን ቡድን መሪው ተናግረዋል።
ዘጋቢ፦ አዲስ ዓለማየሁ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን