
ባሕር ዳር፡ ሰኔ 2/2012 ዓ.ም (አብመድ) በቱሪዝም ዘርፍ የተሰማሩ ተቋማት አገልግሎታቸውን በማስፋፋት እና በማልማት ወቅቱን ወደ መልካም አጋጣሚ እንዲቀይሩ የአማራ ክልል ባሕልና ቱሪዝም ቢሮ አስታውቋል፡፡
የወቅቱ የዓለማችን የጤና ስጋት የኮሮና ቫይረስ ስርጭት የከፋ ጉዳት ካደረሰባቸው የምጣኔ ሀብት ዘርፎች ቱሪዝም ይጠቀሳል፡፡ ቱሪዝም በባህሪው በሰዎች እንቅስቀሴ ላይ የተመሠረተ ነው፡፡ ሃገራት ቫይረሱን ለመከላከል ድንበሮቻቸውን ዝግ ማድረጋቸውን፣ ዜጎችም እንቅስቃሴያቸውን መግታታቸውን ተከትሎ ባለፉት አምስት ወራት የዓለም የቱሪዝም እንቅስቃሴ ሙሉ በሙሉ በሚባል ደረጃ ተቋርጧል፡፡ መረጃዎች እንደሚያመላክቱት በቱሪዝም ዘርፉ በዓለም ዙሪያ ከ100 ሚሊዮን በላይ ዜጎች ሥራ አጥ ሆነዋል፡፡ አፍሪካ እንደ አህጉር ከቱሪዝም ዘርፍ ከምታገኘው ዓመታዊ ጠቅላላ ገቢ ከ52 ነጥብ 8 ትሪሊዮን የአሜሪካን ዶላር በላይ ገቢ ታጣለች ተብሎም ተገምቷል፡፡
በኢትዮጵያም የኮሮና ቫይረስ ስርጭት ከተከሰተበት መጋቢት መጀመሪያ ጀምሮ ቱሪዝሙ ሙሉ በሙሉ ሊባል በሚችል መልኩ ቁሟል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ (ዶክተር) ትናንት በጽሕፈት ቤታቸው ባስተናገዱት 5ኛ ዓመት 5ኛ ልዩ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ስብሰባ ላይ ያረጋገጡትም ይህንኑ ነው፤ ቱሪዝሙ 80 በመቶ ጉዳት ደርሶበታል፡፡ ይህም ኑሯቸውን በቱሪዝም ላይ ለመሠረቱ ወገኖች ጉዳቱ የኅልውና ጉዳይ ሆኗል፡፡
የአማራ ክልል ከጣና ሐይቅ ገዳማት እስከ ጎንደር አብያተ መንግስታት፣ ከስሜን ተራራዎች ብሔራዊ ፓርክ እስከ ላልይበላ ውቅር አብያተ ክርሰቲያናት፣ ከጭስ ዓባይ ፏፏቴ እስከ ግሸን ደብረ ከርቤ፣ ከመቅደላ አምባ እስከ አላጥሽ ብሔራዊ ፓርክ… በርካታ የቱሪስትን ቀልብ የሚስቡ መዳረሻዎች ባለቤት ነው፡፡ በእነዚህ የቱሪስት መዳረሻዎች ላይ ኑሯቸውን የመሠረቱ የኅብረተሰብ ክፍሎች ደግሞ ብዙ ናቸው፡፡
የስሜን ተራራዎች ብሔራዊ ፓርክን የቱሪስት ፍሰት ቀጥተኛ የገቢ ምንጭ አድርገው በማኅበር የተደራጁ እና አገልግሎት ሰጪ ድርጅቶች አሉ፡፡ የፓርኩ ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ አበባው አዛናው ለአብመድ እንደገለጹት በማኅበራት እና አገልግሎት ሰጪ ድርጅቶቹ ውስጥ ከ10 ሺህ በላይ የኅብረተሰብ ክፍሎች አሉ፡፡ ከመጋቢት ወር ጀምሮ ገቢያቸው መቋረጡ ደግሞ ለፓርኩ ኅልውናም አደጋ እንደሆነ አስረድተዋል፡፡ ምክንያቱ ደግሞ የፓርኩ ልማት እና ጥበቃ ከማኅበረሰቡ ተጠቃሚነት ጋር በቀጥታ የተሳሰረ መሆኑ ነው፡፡ ከአስጎብኚ ድርጅት ባለቤቶች መካከል አቶ መላኩ በሪሁን የቱሪዝም ሥራው ሙሉ በሙሉ መቆሙን ጠቅሶ የማኅበራቱን ኅልውና ለማስቀጠል የክልሉ ባሕል እና ቱሪዝም ቢሮ ብድር እንዲያፈላልግ ዝርዝር የሥራ እቅድ አስገብተው ምላሽ እየተጠባበቁ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
የአማራ ክልል ባሕልና ቱሪዝም ቢሮ ኃላፊ ሙሉቀን አዳነ (ዶክተር) በበኩላቸው “አቅም ያላቸውን ማኅበራት ለይቶ ከገንዘብ ተቋማት ጋር ለመነጋገር ዝርዝር የብድር እቅድ ከማኅበራቱ ተቀብለናል” ብለዋል፡፡ ጉዳዩ ገና በሂደት ላይ መሆኑንም አስታውቀዋል፡፡ ቱሪዝሙ የገጠመው ወቅታዊ ችግር እንጂ ዘላቂ ፈተና እንዳልሆነ ያስታወቁት ዶክተር ሙሉቀን ችግሩን እንደመልካም አጋጣሚ ወስዶ ለቀጣይ ሥራ መዘጋጀት እንደሚያስፈልግ ጠቁመዋል፡፡ በቱሪዝም ፍሰቱ ላይ ትኩረት አድርገው የተሠማሩ ተቋማትም ወቅቱን ወደ ጥሩ እድል በመቀየር አገልግሎታቸውን የማስፋፋት እና የማልማት ሥራ እንዲሠሩ ቢሮው ጠቁሟል፡፡
ከቱሪዝሙ መዳከም ጋር ተያይዞ ሥራ ያቆሙ አገልግሎት ሰጪ ድርጅቶችን ለመደገፍ ጥረት እየተደረገ መሆኑንም ዶክተር ሙሉቀን ተናግረዋል፡፡ ይህን አጠናክሮ ለማስቀጠል እና ከወረርሽኙ ማግስት ቱሪዝሙ በፍጥነት የሚያንሠራራበትን የአፈፃፀም ስልት መዘጋጀቱንም አስታውቀዋል፡፡
ዘጋቢ፡- ታዘብ አራጋው
ተጨማሪ መረጃዎችን
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m
ዩቱዩብ https://bit.ly/38mpvDC ያገኛሉ፡፡