ሴቶችን ተጠቃሚ ለማድረግ እየሠራ መኾኑን የአማራ ሴቶች ማኅበር ገለጸ።

35

ደሴ: ነሐሴ 28/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ሴቶች ማኅበር የ2017 አፈጻጸሙን እና የ2018 በጀት ዓመት እቅድ ግምገማ እና ትውውቅ እንደ ወሎ ቀጣና ከዘጠኝ ዞኖች ጋር ለሁለት ቀናት በደሴ ከተማ አካሂዷል።

የኮምቦልቻ ከተማ ሴቶች ማኅበር ጽሕፈት ቤት ኀላፊ እልፍነሽ ደምሴ ኮምቦልቻ ከተማ በተለይም አባላትን በማፍራት እና የበጎ ፈቃድ ሥራዎች ላይ የተሻለ ሥራ መሥራት መቻሉን ተናግረዋል።

በሴቶች ጥቃት እና ሁለንተናዊ ተጠቃማነት ዙሪያ ውስንነቶች ቢኖሩም ከአጋዥ ተቋማት ጋር በመተባበር እየሠሩ መኾናቸውንም ጠቁመዋል።

የኦሮሞ ብሄረሰብ አሥተዳደር ሴቶች ማኅበር ምክትል ቦርድ ሰብሳቢ አንሻ ሺፈራው ሴቶች ላይ በዋናነት በግብርና፣ በጤና እና ጾታዊ ጉዳዮች ዙሪያ የግንዛቤ ፈጠራ ሥራ መሠራቱን ተናግረዋል። ጾታዊ ጥቃት የደረሰባቸውን ከፍትሕ አካላት እና ከአማራ ሴቶች ማኅበር ጋር በመተባበር ድጋፍ እንዲያገኙ ተደርጓል፤ እየተደረገም ይገኛል ነው ያሉት።

በ2017 በጀት ዓመት ከተለያዩ አካላት ወደ 292 ሚሊዮን ብር ድጋፍ በማሰባሰብ ከ3 ሺህ በላይ ሴቶችን የገንዘብ እና የአይነት ድጋፍ እንዲያገኙ እና ካሉባቸው ችግሮች እንዲላቀቁ መሠራቱን የአማራ ሴቶች ማኅበር ዋና ዳይሬክተር ገነት ወንድሙ ገልጸዋል።

ሴቶችን በኢኮኖሚ ተጠቃሚ ለማድረግ ከቀበሌ ጀምሮ ድጋፍ የሚያስፈልጋቸውን መለየት እና ለዚህ የሚኾን የገንዘብ አቅም መፍጠር ላይ በትኩረት እየተሠራ መኾኑን የገለጹት የማኅበሩ ዋና ዳይሬክተር በቀጣይ በጀት ዓመት 5 መቶ ሚሊዮን ብር ለማሰባሰብ መታቀዱን አንስተዋል።

ሴቶች ሰላም በማስፈን የሚጠበቅባቸውን እንዲወጡ ታላሚ በማድረግ እየተንቀሳቀሱ መኾናቸውን አስታውቀዋል።

ዘጋቢ:-ሙሀመድ በቀለ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን

Previous articleየነብዩ ሙሐመድ (ሰ.ዐ.ወ) የትውልድ ቦታ መካ።
Next article“ቦንድ ለልጆቼ እና ለልጅ ልጆቼ ያወረስኩት ታሪክ ነው” የ80 ዓመት እድሜ ባለጸጋው አባት