
የነብዩ ሙሐመድ (ሰ.ዐ.ወ) የትውልድ ቦታ መካ።
ባሕር ዳር፡ ነሐሴ 28/2017 ዓ.ም (አሚኮ) መውሊድ ማለት የነብዩ ሙሐመድ (ሰ.ዐ.ወ) የተወለዱበት ቀን ነው፡፡ ስለነብዩ ሙሐመድ ልደት ሲነሳ ሁሌም አብሮ የሚነሳው የትውልድ ቦታቸው መካ ናት። መካ ታሪካዊ እና ሃይማኖታዊ ከተማ ናት።
መካ በታሪክ “መካህ ኣል-ሙከራማህ” ተብላ ትጠራ የነበረች ከተማ ናት። ከሳዑዲ አረቢያ በስተምዕራብ በኩል ባለው በሒጃዝ ቀጣና ውስጥ የመካ ክፍለ አውራጃ ማዕከልም ናት።
መካ በእስልምና ሃይማኖት ተከታዮች ዘንድ ቅዱስ ከተማ ተብላ ትታወቃለች። የሃይማኖት፣ የታሪክ እና የባሕል ማዕከል እንደኾነች የሚነገርላት ባለ ብዙ ታሪክ ከተማም ናት።
ከታሪክ አኳያ መካ የነብዩ ሙሐመድ የትውልድ ቦታ እና ቁርዓን መጀመሪያ የተገለጠባት ቦታ እንደኾነችም ይታመናል፡፡
ከተማዋ የታላቁ መስጅድ “አልሐራም” እና በእስልምና ሃይማኖት የተከበረው የ’’ካዕባ’’ መገኛም ናት፡፡
“ካዕባ” የተገነባው በነብዩ ኢብራሂም እና በልጃቸው ኢስማኤል እንደኾነ ይነገራል፡፡ መካ ከጥንት ዘመናት ጀምሮ የነበረች ከተማ መኾኗን ጥንተ ታሪኳ ምስክር ነው።
በቁርዓን ውስጥ “ባካህ” ተብላ ትጠራ የነበረ እና ከእስልምና በፊትም የንግድ እና የሃይማኖት እንቅስቃሴ ማዕከል እንደነበረች የሚነገርላት ጥንተዊ ከተማ ናት።
ነብዩ ሙሐመድ (ሰ.ዐ.ወ) የተወለዱበት የቁረይሽ ጎሳ መካን እና ኢኮኖሚዋን የተቆጣጠረ ነበር፤ እነሱም ከእስልምና በፊትም ዓመታዊው የ”ካዕባ” አማኝ ተጓዦች በኩል ትልቅ ገቢ ያገኙ ነበር።
የእስልምና ዘመን ተብሎ በሚጠራው ወቅት እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር በ610 ነብዩ ሙሐመድ (ሰ.ዐ.ወ) በመካ አቅራቢያ ባለው በሒራ ዋሻ ውስጥ የእስልምና ሃይማኖት መሠረት የኾነውን ቁርዓንን ተቀብለዋል።
ከዚያም በኋላ በእርሳቸው እና በተከታዮቻቸው ላይ ከሚደርሰው ግፍ የተነሳ ከተከታዮቻቸው ጋር በ622 ወደ መዲና ሄዱ።
ነገር ግን በ630 ነብዩ ሙሐመድ (ሰ.ዐ.ወ) እና ተከታዮቻቸው መካን እና “ካዕባ”ንም ከጣኦቶች አንጽተው እስልምናን በከተማዋ መሠረት እንዲኖረው አድርገዋል።
መካ በመካከለኛው ዘመን ውስጥ የእስልምና ትምህርት እና የሃይማኖት ተጓዦች ማዕከል ኾና የኖረች ከተማ ናት።
ከተማዋ በተለያዩ የእስላማዊ ካሊፋቶች ማለትም በመጀመሪያ የዑማያውያን፣ በኋላ የአባሲያውያን ከዚያም የኦቶማን ኢምፓየር መንግሥታት መቆጣጠርን ያስተናገደች ከተማ ናት።
በዘመናዊ የታሪክ ምዕራፏ ላይ እያለች በ1925 ኢብን ዳውድ መካን አዲስ ወደ ተቋቋመው የሳውዲ አረቢያ መንግሥት እንድትጠቃለል አድርጓታል።
ከዚያን ጊዜ ጀምሮ የሳዑዲ አረቢያ መንግሥት ከፍተኛ የዘመናዊ ልማት ፕሮጀክቶችን በማከናወን ቁጥሩ ከፍ ላለ የሃይማኖት ተጓዦች ቦታ እንዲበቃ የመስጂድ አልሐራም ማስፋፊያ ሥራዎችን አጠናክረው ቀጥለው አሁን ላለው ጊዜ መሠረት ጥለዋል።
መካ በእስልምና ሃይማኖት ውስጥ ያላት ሚና ሲገለጽ የእስልምና መንፈሳዊ ልብ ናት ማለት ይቻላል።
በዓለም ዙሪያ ያሉ ሁሉም ሙስሊሞች ሲጸልዩ የሚመለከቱት አቅጣጫ የኮነችው የ‘’ካዕባ’’ መገኛ ናት።
በከተማዋ በየዓመቱ የሚካሄደው የሐጂ ጉዞ ከእስልምና አምስቱ መሠረቶች አንዱ ሲኾን ማንኛውም ችሎታ ያለው አንድ ሙስሊም በሕይዎት ዘመኑ ቢያንስ አንድ ጊዜ መሄድ እንዳለበት የሃይማኖቱ አስተምህሮ ኾኖ ተቀምጧል።
በተጨማሪም ቦታው በዓመቱ በማንኛውም ጊዜ ሊከናወን በሚችል የዑምራ ጉዞ ሚሊዮኖችን ለጉብኝት የሚስብ እና የሚጋብዝ ስፍራ ነው።
በመካ ከተማ የሚገኘው መስጅድ አልሐራም በእስልምና ሃይማኖት ተከታዮች ዘንድ ቅዱስ ስፍራ ሲኾን በየዓመቱ በሚሊዮን የሚቆጠሩ የሃይማኖቱ ተከታዮች የሚስተናገዱበት የሐጂ እና ዑምራ ጉዞ የሚደረግበት ዋና ቦታ ነው፡፡
“ካዕባ” ማለት ደግሞ በመስጅድ አልሐራም መካከል ላይ ያለች የኩብ ቅርፅ ያላት ቦታ ናት። በእስልምና ውስጥ በጣም የተቀደሰች ቦታ ተደርጋ ትቆጠራለች።
የሃይማኖት ተጓዦች በሐጂ እና በዑምራ ሂደት ውስጥ የተካተተ በ”ካዕባ” በዙሪያው በመዞር የሚፈጸም መሠረታዊ ሥርዓት ”ታዋፍ” ተብሎ ይጠራል።
የመስጂዱ ዙሪያ ሰፊ ሲኾን ይህም በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ተከታዮች እንዲቀመጡ እና እንዲሰግዱ የተመቸ ነው።
መካ በርካታ ቁጥር ያለው ሕዝብ የሚኖርባት ከተማ ስትኾን በሕዝብ ብዛቷ በሳዑዲ አረቢያ ከሚገኙ ከተሞች ከሪያድ እና ከጂዳ ቀጥላ በሦስተኛነት ተቀምጣለች፡፡
በየዓመቱም በሐጂ እና ዑምራ ጉዞ በሚሊዮን የሚቆጠሩ የሃይማኖት ተጓዦችን ታስተናግዳለች፡፡
ምንም እንኳ የሳዑዲ አረቢያ ኢኮኖሚ በነዳጅ ሃብት ላይ የተመሠረተ ቢኾንም የሃይማኖት ቱሪዝም በመካ ኢኮኖሚ ላይ አስተዋጽኦው ጉልህ ነው።
የሃይማኖት ተጓዦች ለአካባቢው የንግድ ሥራዎች በተለይም ሆቴሎች፣ የምግብ እና የትራንስፖርት አገልግሎቶች ትልቅ አስተዋጽኦ ያደርጋሉ።
በሐጂ ወቅት ብቻ በቢሊዮን ዶላር ገቢ ይገኛል። በዚህም በሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎች የሥራ ዕድል ይፈጠርላቸዋል፡፡
በመካ ዋና ዋና የኢኮኖሚ ሴክተር ተብለው የሚጠቀሱት የሆቴል እና መስተንግዶ ተቋማት፣ ንግድ እና የትራንስፖርት ዘርፎች ሲኾኑ በዚህ ጉዞ ቀጥተኛ ተሳታፊ እና ተጠቃሚዎች ናቸው፡፡
ምንጭ፦ ወርልድ ሂስትሪ እና ሌሎች ድረ ገጾችች
ዘጋቢ: ፍሬሕይወት አዘዘው
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን