
ደብረ ማርቆስ: ነሐሴ 28/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ወይዘሮ ቀለሟ ጌታቸው ነዋሪነታቸው በደብረ ማርቆስ ከተማ ነው። ግለሰቧ ጠላ ጠምቀው በመሸጥ የሚኖሩበት ደሳሳ ጎጇቸው ጣራው በማርጀቱ እያፈሰሰ በችግር ውስጥ ከልጆቻቸው ጋር ሰባት ዓመታትን አሳልፈዋል።
የወይዘሮ ቀለሟ መኖሪያ ቤት ክረምት በመጣ ቁጥር በውስጡ ለመቀመጥም ኾነ ውሎ ለማደር አስቸጋሪ ከመኾኑ በላይ ጠላ ጠምቀው በመሸጥ የሚተዳደሩበትን ሥራ በማከናወን የእለት ተዕለት ሕይወታቸውን ለመምራት ፈተና ኾኖባቸው ቆይቷል።
ዛሬ ላይ ግን የምሥራቅ ጎጃም ዞን ሥራና ክህሎት መምሪያ ሠራተኞች ከደመወዛቸው ገንዘብ በማሠባሠብ በሠሩት መልካም ሥራ ወይዘሮ ቀለሟ እና ቤተሰባቸው ይኖሩበት የነበረው ቤት በአዲስ መልኩ በመታደሱ መደሰታቸውን ተናግረዋል።
በጎ ፈቃድ ለሌሎች መድረስ ነው ያሉት የበጎ ፈቃድ ተሳታፋዎች፣ አቅም የሌላቸው ወገኖች ካለባቸው ችግር ወጥተው የተሻለ ሕይወት እንዲኖሩ በማሰብ ባከናወኑት በጎ ተግባር ከፍተኛ የህሊና ርካታ እንደተሰማቸው ገልጸዋል።
የምሥራቅ ጎጃም ዞን ሥራና ክህሎት መምሪያ ተወካይ ኀላፊ ሰሎሞን አለልኝ 60 የሚኾኑ የተቋሙ ሠራተኞች ባደረጉት የገንዘብ እና የጉልበት አስተዋጽኦ በተሠራው መልካም ሥራ አቅም የሌላቸውን ሰዎች ቤት በመጠገን በጎነትን በተግባር ማረጋገጥ መቻሉን ገልጸዋል።
መምሪያው በየወረዳው በማስተባበር በክረምት የመማሪያ ቁሳቁስ በማሠባሠብ በበጎ ፈቃደኝነት ደም ከመለገስ በተጨማሪ ከ1 ነጥብ 3 ሚሊዮን ብር በላይ የፈጀ የበጎ ፈቃድ ሥራዎች መከናወናቸውን ተናግረዋል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን