
ደሴ: ነሐሴ 28/2017 ዓ.ም (አሚኮ) አርሶ አደር ሙሀመድ ጁሀር በደቡብ ወሎ ዞን ጃማ ወረዳ የ08 ቀበሌ ነዋሪ ናቸው። ባለፉት ዓመታት ከጓደኞቻቸው ጋር ስንዴን በኩታ ገጠም የማምረት ተሞክሮ አላቸው።
አርሶ አደሩ ሰብልን በኩታ ገጠም መዝራት ከጀመሩ ወዲህ ከአንድ ሄክታር ከ45 እስከ 50 ኩንታል ምርት በማምረት ከቤተሰባቸው ፍጆታ አልፈው ለገበያ እያቀረቡ መኾኑን ገልጸዋል።
ሰብልን በኩታ ገጠም መዝራት ከእርሻ ዝግጅት እስከ ሰብል ስብሰባ በተመሳሳይ ሰዓት ሥራን በመከወን በአርሶ አደሮች መካከል የልምድ ልውውጥ እና ውድድር እንዲኖር ምቹ ኹኔታን የሚፈጥር መኾኑንም አብራርተዋል።
በዚህ ዓመት የዘሩትን የስንዴ ሰብል ለፍሬ ለማብቃት የመጀመሪያ ዙር የአረም እና የተባይ አሰሳ ሥራ እያከናወኑ መኾናቸውን ገልጸዋል።
ሌላኛው አርሶ አደር ከቤ አሸናፊ ምርጥ ዘርና ማዳበሪያ በአግባቡ በመጠቀም በኩታ ገጠም መዝራት ከጀመሩ ወዲህ የተሻለ ምርት በማምረት ኑሯቸው እየተሻሻለ መምጣቱን አንስተዋል።
ሰብልን በኩታ ገጠም በመዝራት ከአንድ ሄክታር እስከ 55 ኩንታል ስንዴ እያመረቱ መኾኑንም ተናግረዋል። በቀጣይ ከዚህ የተሻለ ለማምረት በትኩረት እየሠሩ መኾኑን ጠቁመዋል።
የ06 ቀበሌ ነዋሪ የኾኑት አርሶ አደር በላይ ኀይልዬ ሰብልን በኩታ ገጠም መዝራት የአርሶ አደሮችን ምርት እና ምርታማነት በመጨመር ኑሮው እንዲሻሻል ያግዛል ብለዋል።
የጃማ ወረዳ ስንዴ አምራች እና ለሰብል ልማት ሥራ ምቹ በመኾኑ በወረዳው የዘር ብዜት የምርምር ማዕከል፣ የማጨጃ እና የመውቂያ ማሽን እንዲኹም የጸረ ተባይና የአረም ማጥፊያ መድኃኒት በተመጣጣኝ ዋጋ እንዲቀርብላቸውም ጠይቀዋል።
የጃማ ወረዳ ግብርና ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ኀይሉ አሰፋ በወረዳው 40 ሺህ 200 ሄክታር የሚታረስ መሬት መኖሩን አንስተው ከዚህ ውስጥ 40 ሺህ 79 ሄክታር መሬት በተለያዩ ሰብሎች በዘር ተሸፍኗል ነው ያሉት።
በ2017/2018 የመኸር የምርት ዘመን በወረዳው 25 ሺህ 993 ሄክታር መሬቱ በስንዴ መሸፈኑን ተናግረው ከዚህ ውሰጥ 22 ሺህ ሄክታር መሬት በ17 ቀበሌዎች አርሶ አደሮችን በ139 የስንዴ ክላስተር በማደራጀት በኩታ ገጠም የተሸፈነ መኾኑን ተናግረዋል።
ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ ግብዓት በአግባቡ መጠቀም ወሳኝ በመኾኑ በ2017/2018 የመኸር ዘመን 98 ሺህ ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ እና 38 ሺህ 989 ኩንታል ስንዴ ምርጥ ዘር መጠቀም መቻሉን አንስተዋል።
በምርት ዘመኑ ከአንድ ሄክታር 46 ኩንታል ስንዴ በማምረት ከዚህ በፊት ይመረት ከነበረው አራት ኩንታል ጭማሪ ለማምጣት በእቅድ ተይዞ ወደ ሥራ መገባቱንም አቶ ኀይሉ ተናግረዋል።
እቅዱን ሊያሳኩ እና ምርታማነትን ሊጨምሩ የሚችሉ የአረም ሥራ፣ የተባይ አሰሳ እና ሌሎችም ተግባሮች እየተከናወኑ መኾናቸውንም ገልጸዋል።
በምርት ዘመኑ በጃማ ወረዳ 1 ነጥብ 5 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ለማምረት በእቅድ ተይዞ ወደ ሥራ መገባቱን የጠቆሙት ኀላፊው ከዚህ ውስጥ1 ነጥብ 2 ሚሊዮን ኩንታሉ በስንዴ የሚሸፈን ነው ብለዋል።
በአርሶ አደሮች የሚነሱ የግብዓት ማሳደጊያ ቴክኖሎጂዎች እንዲሟሉ ለሚመለከተው አካል ጥያቄ መቅረቡን አቶ ኀይሉ ተናግረዋል።
በደቡብ ወሎ ዞን በ2017/18 የምርት ዘመን 432 ሺህ ሄክታር በላይ መሬትን በማልማት 15 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ለመሰብሰብ ታቅዶ እየተሠራ መኾኑን የዞኑ ግብርና መምሪያ የሰብል ልማት ቡድን መሪ ይመር ሰይድ ተናግረዋል።
222 ሺህ ሄክታር የሚኾን ማሳ በስንዴ በዘር ለመሸፈን ታቅዶ 218 ሺህ ሄክታር መሬት በስንዴ ዘር መሸፈኑን እና ከዘጠኝ ሚሊዮን ኩንታል በላይ የስንዴ ምርት ይገኛል ተብሎ እንደሚጠበቅም ቡድን መሪው ገልጸዋል።
የዞኑን ምርታማነት ባለፈው ከነበረው በሄክታር 31 ኩንታል ምርት በዚህ ዓመት 35 በሄክታር ኩንታል ለማምረት መታቀዱንም አቶ ይመር ተናግረዋል።
የዞኑን ምርትና ምርታማነት ለመጨመር ይረዳ ዘንድ 519 ሺህ ኩንታል ማዳበሪያ ተሰራጭቷል ያሉት አቶ ይመር አሲዳማ አፈርን ለማከም 7 ሺህ 613 ኩንታል ኖራ ጥቅም ላይ መዋሉንም አስታውሰዋል።
ከ18 ሺህ ኩንታል በላይ የልዩ ልዩ ሰብሎች ምርጥ ዘር መሰራጨቱንም አመልክተዋል። እስካሁን 424 ሺህ 600 ሄክታር መሬት በዘር የተሸፈነ ሲኾን ከዚህም 228 ሺህ ሄክታር መሬቱ የተሸፈነው በዋና ዋና ሰብሎች ማለትም በስንዴ፣ በጤፍ፣ ማሽላ፣ ቦለቄና ማሾ ሰብሎች ናቸው።
አጠቃላይ የዞኑ ሰብል በጥሩ ቁመና ላይ ይገኛል ያሉት አቶ ይመር የታቀደው ምርት እንደሚገኝ አመላካች መኾኑንም አንስተዋል።
መረጃው የጃማ ወረዳ የመንግሥት ኮሙኒኬሽን ነው።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን