
ጳጉሜን 02/2017 ዓ.ም በኢትዮጵያ ሙሉ የጨረቃ ግርዶሽ እንደሚከሰት መጋቢ ሐዲስ ሮዳስ ታደሰ (ዶ.ር) ገለጹ።
አዲስ አበባ፡ ነሐሴ 28/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ጳጉሜን 02/2017 ዓ.ም በመላዉ ኢትዮጵያ እና የአፍሪካ አህጉር ሙሉ የጨረቃ ግርዶሽ እንደሚከሰት የአንድሮሜዳ የምርምር ተቋም መሥራች እና ኃላፊ መጋቢ ሐዲስ ሮዳሥ ታደሰ (ዶ.ር) ገልጸዋል።
ክስተቱ ለኢትዮጵያ የመቃናት እና የልዕልና ዓመት ማሳያ እንደሚሆንም እምነታቸው ገልጸዋል። ኢትዮጵያውያን እና አፍሪካውያን ሁነቱን እንዲከታተሉም ጥሪ አቅርበዋል።
ግርዶሽ ማለት አንድ አካል ሌላዉ እንዳይታይ የመሸፈን ወይንም የመጋረድ ክስተት ነዉ። የጨረቃ ግርዶሽ የሚከሰተው ጨረቃ፤ መሬትና ጸሐይ በሚያደርጉት መስተጋብር ነው። ፀሐይ፣ መሬት እና ጨረቃ በሰልፍ ሲሰደሩ ግርዶሽ የተሰኜዉ የተፈጥሮ ክስተት ይፈጠራል። ይህም ማለት መሬት በፀሐይና በጨረቃ መካከል ድንገት ስትደነቀር ነው ብለዋል። በዚህን ጊዜ ወደ ጨረቃ የሚሄደው የፀሐይ ብርሃን በምድር ይጋረዳል ነው ያሉት።
ምድር በፀሐይና ጨረቃ መካከል መደንቀር ደግሞ አንዳች ጥላ እንዲፈጠር ያደርጋል። ያን ጊዜ ጨረቃ በተፈጠረው ጥላ መካከል ማለፍ ስትጀምር የጨረቃ ግርዶሽ ተፈጠረ እንላለን ብለዋል።
በዚህም ምክንያት ጳጉሜን 02/2017 ዓ.ም በኢትዮጵያ በ13ኛዋ ወር የ13ኛዋ ጨረቃ ሙሉ ግርዶሽ በመላ አፍሪካ አህጉር፤ እስከ አዉስትራሊያና እስያ አህጉሮች ድረስ ቢሊዮኖች የሚመለከቱት ሙሉ የጨረቃ ግርዶሽ ይከሰታል ነው ያሉት።
ግርዶሹ እሁድ ማታ ጳጉሜ 02/ 2017 ዓ.ም ከምሽቱ 12:28 ጀምሮ እንደሚከሰት ገልጸዋል። ያኔ ፀሐይ በስተምዕራብ አድማስ፣ ጨረቃ ደግሞ በስተምሥራቅ አድማስ እንደምትሆንና የፀሐይ ብርሃን ሙሉ በሙሉ ሲያርፍባት ሙሉ እንደምትሆን ተንትነዋል። በሰዓቱ መሬት በመካከል እንደምትገባ አንስተዋል።
በዕለቱ ሦስት ዓይነት የጨረቃ ግርዶሽ እንደሚከሰትም አብራርተዋል። 12:28 መሬት ጨረቃን መጋረድ ትጀምራለች፤ ያኔ አንደኛዉ ድብዙዙ የጨረቃ ግርዶሽ ይከሰታል፤ ከምሽቱ 1:27 ግርዶሽ እና ከምሽቱ 2:30 ደግሞ ሙሉ የጨረቃ ግርዶሹ ይከሰታል ነው ያሉት። ያኔ ጨረቃ የደም ቀለም ትላበሳለች ብለዋል። ከምሽቱ 3:11 ደቂቃ ደግሞ ጨረቃ በጣም ቀልታ የምታታይበት ሰዓት እንደኾነ ገልጸዋል። ከምሽቱ 3:52 ግርዶሹ የሚያበቃበት ሰዓት እንደሆነም ተናግረዋል።
በአዲሱ ዓመት ዋዜማ ኢትዮጵያዊያን ክስተቱን ቀና ብለዉ እንዲመለከቱ ምክንያት የሆነዉ ይህ አስደናቂ የተፈጥሮ ክስተት ዓመታቸዉ የተቃና፤ ያማረ እና ለኢትዮጵያም የመቃናት እና የልዕልና ዓመት እንደሚኾን እምነታቸውን ገልጸዋል።
ዘጋቢ፦ በለጠ ታረቀኝ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!