የጤና ጣቢያዎችን የተሻለ አፈጻጸም ማስፋት ይገባል።

6

ባሕር ዳር፡ ነሐሴ 28/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የጤና ዘርፍ የሥራ ኀላፊዎች እና ባለሙያዎች በባሕር ዳር የሚገኙ የጤና ተቋማትን ጎብኝተዋል።

በሀን ጤና ጣቢያ ጉብኝት ያደረጉት በደቡብ ወሎ ዞን የወረባቦ ወረዳ ጤና ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ሰለሞን አደም በርካታ ሥራዎችን እንደጎበኙ ገልጸዋል።

በጤና ጣቢያው የንጽሕና አጠባበቅ፣ የሕክምና አገልግሎት አሰጣጡ እና መረጃን በዲጂታላይዝድ ለመያዝ የተሠሩ ሥራዎች የሚያስተምሩ መኾናቸውንም አንስተዋል።

“ጉብኝቱ በየወረዳችን መሰል ሥራ እንድንሠራ ያነሳሳል” ያሉት አቶ ሰለሞን ወረዳዎችም በተመሳሳይ ደረጃ እንዲደርሱ ድጋፍ እና ክትትል እንደሚያስፈልግ ነው የገለጹት።

ሌላው በጉብኝቱ የተሳተፉት የባሕር ዳር ዙሪያ ጤና ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ዳንኤል በሁሉ ወረቀት አልባ የኾነ የአገልግሎት አሰጣጥን መጎብኘታቸውን ገልጸዋል።

የተመለከቱትን ውጤታማ ሥራ ወደ ወረዳቸው ወስደው እንደሚተገብሩትም ተናግረዋል።

ሁሉም የጤና ተቋማት መሰል አገልግሎት በመስጠት እና መሠረተ ልማት እና ቁሳቁስን በማሟላት የሕክምና አገልግሎትን ማሳደግ እንደሚገባም አንስተዋል።

በደቡብ ጎንደር ዞን የሊቦ ከምከም ወረዳ ጤና ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ሲስተር ወርቅነሽ አካሉ በጉብኝታቸው አዲስ ነገር ማግኘታቸውን ገልጸዋል።

ከቦርድ ጀምሮ እስከ ጤና ጣቢያ ድረስ ያለው ቅንጅታዊ አሠራር እና የባለሙያዎች ቁርጠኝነት ለውጤታማነት ያለውን አበርክቶ ማስተዋላቸውንም ጠቁመዋል።

የከተማ አሥተዳደሩ በጤና ጣቢያው ላይ ያለውን ድጋፍም መመልከታቸውንም አስረድተዋል።

የአማራ ክልል ጤና ቢሮ ምክትል ኀላፊ ገስጥ ጥላሁን የጉብኝቱ ዓላማ በ2017 በጀት ዓመት የተፈጸሙ ተግባራት ምን ያክል ውጤታማ እንደኾኑ ለመለካት መኾኑን ገልጸዋል።

በበጀት ዓመቱ 83 በመቶ የሚኾነው ሕዝብ የተገለገለው በጤና ጣቢያዎች መኾኑንም ጠቅሰዋል።

ከተጎበኙት ተቋማት መልካም ተሞክሮን በመውሰድ፣ የሚጎድላቸውን በመጠቆም እና በመወያየት ለቀጣይ የጤና አገልግሎት ትምህርት ለመውሰድ እንደሚያስችልም ተናግረዋል።

ባለፈው የበጋ ወራት የደብረ ብርሃንን ጤና ጣቢያዎች የተሻለ አፈጻጸም በማስጎብኘት እና ንቅናቄ በመፍጠር ተሞክሮውን ለማስፋት ቃል መገባቱንም አስታውሰዋል።

በንቅናቄውም 56 የጤና ተቋማት ከነበሩበት ደረጃ ተሻሽለው ሞዴል መኾናቸውን አንስተዋል።

የሀን እና የባሕር ዳር ጤና ጣቢያዎችም ከደብረ ብርሃን ንቅናቄ በኋላ የበለጠ መሥራታቸውን ጠቁመዋል።

ዘጋቢ፦ ዋሴ ባየ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን

Previous articleበሕዳሴው ግድብ ላይ የታየው የአንድነት መንፈስ በሌሎች ሀገራዊ ጉዳዮች ላይም ሊደገም ይገባል።
Next article“የታላላቆቻችንን በዓል የምናከብረው የእነርሱን አርአያ ለመከተል ምክንያት እንዲሆነን ነው” ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር)