በሕዳሴው ግድብ ላይ የታየው የአንድነት መንፈስ በሌሎች ሀገራዊ ጉዳዮች ላይም ሊደገም ይገባል።

3

በሕዳሴው ግድብ ላይ የታየው የአንድነት መንፈስ በሌሎች ሀገራዊ ጉዳዮች ላይም ሊደገም ይገባል።

ባሕር ዳር፡ ነሐሴ 28/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የኢትዮጵያውያን አንድነት የታየበት እና የአፍሪካውያን ጭምር ኩራት የኾነው የታላቁ የኢትዮጵያ የሕዳሴ ግድብ ሊመረቅ ጥቂት ጊዜ ቀርተውታል።

ግድቡ ከዚህ እንዲደርስ መላው ኢትዮጵያውያን ሀብታቸውን እና ላባቸውን አፍስሰውበታል። በዓድዋ የታየው አርበኝነትም በዚህ ትውልድ ዳግም ተደግሟል።
በወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን የሁመራ ከተማ ምክትል ከንቲባ እና የንግድና ገበያ ልማት ጽሕፈት ቤት ኀላፊ በላይ ፈለቀ እንዳሉት በመላው ኢትዮጵያውያን የተባበረ ክንድ የተገነባው ግድብ የቀደምት አባቶች የመተባበር መንፈስ የታየበት፣ ለቀጣዩ ትውልድ ደግሞ ትልቅ መነሳሳት የፈጠረ ነው።

በራስ አቅም መልማትን ያሳየ፣ የአይቻልም መንፈስን የሰበረ እና የአሸናፊነት ካባን ያጎናጸፈ ሐውልት መኾኑንም ገልጸዋል።

ግድቡ በርካታ ኢትዮጵያውያንን ከጨለማ የሚያላቅቅ በተለይም ደግሞ ከግብርና ወደ ኢንዱስትሪ መር የሚደረገውን ሽግግር የሚያፋጥን መኾኑንም አንስተዋል።

ኢትዮጵያ የኀይል አቅርቦቷን ከማሟላት ባለፈ ለጎረቤት ሀገራት ጭምር የኀይል አማራጭ በማቅረብ የውጭ ምንዛሬ ለማገኘት አቅም የሚፈጥር መኾኑንም ነው የገለጹት።

ሌላኛው አስተያየት ሰጭ የደቡብ ወሎ ዞን መንገድ መምሪያ ኀላፊ ኢብራሂም ሀሰን ግድቡ ዓባይን ከእንጉርጉሮ እና ከተረት ወደ ሚጨበጥ ዳቦ መቀየር ችሏል ብለዋል።

ዓባይ የዲፕሎማሲ አቅም የታየበት እና ሌሎች ታላላቅ የልማት ሥራዎችን ለመሥራት ያነሳሳ መኾኑንም ገልጸዋል።

ድንበር ተሻጋሪ ወንዞችን የሚጋሩ ሀገራትም ሀብቱን በዕኩልነት የመጠቀም መብት እንዳላቸው ያሳየ እንደኾነም ጠቁመዋል።

ለግድቡ እውን መኾን ደግሞ የዞኑ ሕዝብ ግድቡ ከተጀመረበት ጊዜ ጀምሮ እስከ አሁን ከትንሽ እስከ ትልቅ፣ ከድሃ እስከ ባለጸጋ ሁሉን አቀፍ አሻራውን አሳርፏል ብለዋል።

በቀጣይም ማኅበረሰቡ ለግድቡ መጠናቀቅ ሃብቱን እንዳበረከተው ሁሉ ግድቡ ለደለል እና መሰል ችግሮች እንዳይጋለጥ በተፋሰስ ልማት ላይ ሊያተኩር ይገባል ነው ያሉት።

የምዕራብ ጎጃም ዞን ሲቪል ሰርቪስ እና የሰው ኃብት ልማት መምሪያ ኀላፊ የሻረግ ታፈረ እንደገለጹት ደግሞ የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የኢትዮጵያን ከፍታ ያረጋገጠ እና የይቻላል ስሜትን ያሳየ ነው።

ዞኑ የዓባይ ወንዝ መነሻ በመኾኑ ማኅበረሰቡ ለግድቡ የነበረው አስተዋጽኦ ከፍተኛ እንደነበር ገልጸዋል። በተለይም ደግሞ ሴቶች በአደረጃጀቶቻቸው ጭምር ልዩ አሻራ ጥለዋል ብለዋል።

በታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ላይ የታየው አንድነት እና መተባበር በሌሎች ሀገራዊ የልማት እና የመልካም አሥተዳደር ሥራዎች ላይም ሊደገም ይገባል ነው ያሉት።

ዘጋቢ፦ ዳግማዊ ተሠራ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን

Previous articleየኅብረት ሥራ ማኅበራት ሪፎርሙ ጠንካራ፣ ተወዳዳሪ እና አካታች ማኅበራትን ለመፍጠር አግዟል።
Next articleየጤና ጣቢያዎችን የተሻለ አፈጻጸም ማስፋት ይገባል።