
አዲስ አበባ፡ ነሐሴ 28/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ኢትዮጵያ ታላቁን ፕሮጀክት የሕዳሴ ግድብን ልታስመርቅ ሸር ጉድ እያለች ነው።
ከአሚኮ አዲስ ኤፍ ኤም 103 ነጥብ 5 ጋር ቆይታ ያደረጉት በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውጭ ግንኙነት እና የሰላም ቋሚ ኮሚቴ አባል አምባሳደር ዲና ሙፍቲ በታላቁ የኢትዮጵያ የሕዳሴ ግድብ ዙሪያ በርካታ ችግሮች እንደነበሩ አንስተዋል።
አምባሳደር ዲና ሙፍቲ በዓባይ ወንዝ ዙሪያ የነበረው የባለቤትነት የተሳሳተ ትርክት እና ፖለቲካ ኢትዮጵያን ጨምሮ የላይኛው ተፋሰስ ሀገራትን ያገለሉ ውሎች እንዲኖሩ አድርጓል ይላሉ።
በዓባይ ዙሪያ የተፈረሙ ቀደምት ውሎች ከተሳሳተ ትርክት፣ ግንዛቤ፣ ከተሳሳተ ፍላጎት የመነጩ እና የቅኝ ገዥ ሀገራት ጫና ጎልተው የታዩባቸው ውሎች መኾናቸውን አምባሳደር ዲና ሙፍቲ አንስተዋል።
የዓባይ ወንዝ 85 በመቶ ባለቤት የኾነችው ኢትዮጵያ ከወንዙ በፍትሐዊነት ልጠቀም በሚል በ2003 ዓ.ም መጋቢት ወር የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ መሠረት ስትጥል ፈተናዎች ከፍ ብለው መታየት መጀመራቸውንም ጠቁመዋል።
የታላቁ የኢትዮጵያ የሕዳሴ ግድብ ባለፉት 14 ዓመታት በብዙ ፈተና የተፈተነ እና ፈተናውን ያለፈ ታላቅ ፕሮጀክት እንደኾነም አስረድተዋል።
አምባሳደር ዲና ስለሂደቱ ሲናገሩ የግድቡ ጥንስስ ሲጀመር ኢትዮጵያ ግድቡን መሥራት አትችልም ውሸት ነው የሚል ነበር፤ ከተጀመረ በኋላ ደግሞ የመሥራት አቅም የላትም ከማለት ተሻግሮ ኢትዮጵያ ላይ ክሶች መጀመራቸውን ነው ያብራሩት።
ኢትዮጵያ በበኩሏ በጋራ መሥራት እና በጋራ እንጠቀም የሚለውን ሀሳቧን ማስተጋባቷን ነው አምባሳደር ዲና የገለጹት።
በግድቡ ምክንያትም የፖለቲካዊ፣ የኢኮኖሚያዊ፣ የዲፕሎማሲያዊ እና የማኅበራዊ ውጣ ውረዶች ታልፈዋል ነው ያሉት። የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የኢትዮጵያውያን ዳግም ዓድዋ ነው ብለዋል።
የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ መጠናቀቅ ለኢትዮጵያውያን ትርጉሙ የገዘፈ እንደኾነ የሚያነሱት አምባሳደር ዲና ሙፍቲ ግድቡ ትብብር፣ አንድነት እና መደጋገፍ ምን አይነት ተአምራዊ ውጤት እንደሚያመጣ ማሳያ እንደኾነም አስገንዝበዋል።
ኢትዮጵያ በዲፕሎማሲውም በእጅጉ አሸናፊ የኾነችበት እንደኾነ እና ድንጋይ ለወረወረ ድንጋይ ከመወርወር ይልቅ በትዕግስት ነገሮችን ማየት ለድል እንደሚያበቃም የተማረችበት መኾኑንም ጠቁመዋል።
አምባሳደር ዲና ሙፍቲ ግድቡ ኢትዮጵያ ትላልቅ ፕሮጀክትን የመሥራት አቅም እንዳላትም ትምህርት የተወሰደበት ነው ብለዋል።
ዘጋቢ፦ ቴዎድሮስ ኃይለኢየሱስ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን