በደቅ ደሴት የተገነባው ወደብ የጎብኝዎችን እንቅስቃሴም ያሳድጋል።

6

በደቅ ደሴት የተገነባው ወደብ የጎብኝዎችን እንቅስቃሴም ያሳድጋል።

ባሕር ዳር: ነሐሴ 28/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የጣና ሐይቅ የጥበብ፣ የእምነት እና የታሪክ ማኅደር ሲኾን አያሌ ተፈጥሯዊ እና ሰው ሠራሽ መዳረሻዎችም አሉት። በጣና ሐይቅ ውስጥ ከሚገኙት ደሴቶች መካከል ደግሞ ደቅ ደሴት አንዱ ነው።

በውኃ ለተከበበችው የደቅ ደሴት ብቸኛው የትራንፖርት አማራጯ የባሕር ላይ ትራንስፖርት ነው። ለደቅ ደሴት በቂ የትራንስፖርት አገልግሎት የሚሰጥ ወደብ ባለመኖሩ የደሴቲቷ ነዋሪዎች ለችግር ተዳርገው ቆይተዋል። ይህንን መነሻ በማድረግ ነዋሪዎች ወደብ እንዲገነባላቸው ለዘመናት ሲጠይቁ ቆይተዋል።

የአማራ ክልል ባሕል እና ቱሪዝም ቢሮ የአካባቢውን የቱሪዝም ጸጋ መሠረት በማድረግ ከ21 ሚሊዮን ብር በላይ በኾነ ወጭ የወደብ ግንባታ እና የመሸጋገሪያ ድልድይ መገንባቱን አስታውቋል።

የቢሮው የቱሪዝም ልማት ዳይሬክተር መልካሙ አዳም የተገነባው ወደብ 8 ሜትር ስፋት እና 37 ሜትር ርዝመት ያለው ደረጃውን የጠበቀ መኾኑን ገልጸዋል።

በአሁኑ ወቅትም ወደቡ ለነዋሪዎች አገልግሎት እየሰጠ ስለመኾኑም ተናግረዋል። ወደቡን ገንብቶ ወደ ሥራ ለማስገባት የኅብረተሰቡ ተሳትፎ የጎላ አስተዋጽኦ እንደነበረውም አመላክተዋል።

የወደቡ ግንባታ በ1337 ዓ.ም እንደተመሠረተች ለሚነገርላት ለፈለገ ሕይዎት ጣና ሐይቅ ቅድስት አርሴማ ገዳምን የጎብኝዎች መዳረሻ ለማድረግ ትልቅ አስተዋጽኦ እንደሚያደርግ ነው አቶ መልካሙ የገለጹት፡፡

በጣና ሐይቅ የሚገኙ የቱሪዝም መዳረሻዎችን ለማስተሳሰር ሚናው የጎላ መኾኑንም ጠቁመዋል። ለክልሉ የቱሪዝም እንቅስቃሴም ተጨማሪ አቅም እንደኾነ ነው ዳይሬክተሩ ያብራሩት።

በፈለገ ሕይዎት ጣና ሐይቅ ቅድስት አርሴማ ገዳም የሰበካ ጉባኤ ጸሐፊ ቄስ ደመቀ አስናቀው በፊት ጎብኝዎች በናርጋ ሥላሴ እና በጉረር ቀበሌ በሚገኙት ወደቦች ይጠቀሙ እንደነበር አንስተዋል። ይህም ከፍተኛ እንግልት ይፈጥር እንደነበር ነው የሚገልጹት።

የተገነባው ወደብ ለብዙ ዘመናት ሲጠየቅ የቆየውን ጥያቄ የመለሰ እና በጥሩ ኹኔታ የተሠራ ስለመኾኑም ተናግረዋል። ወደ ገዳሟ ለሚመጡ ምዕመናን እና ሌሎች ጎብኝዎች ተጨማሪ የጉብኝት እድል እንደሚፈጥር አመላክተዋል።

ለነዋሪዎቿ ደግሞ የትራንስፖርት እፎይታን የሰጠ ስለመኾኑም ነው የገለጹት። ገዳሟን ለሚጎበኙ ጎብኝዎች ምቹ ኹኔታን የሚፈጥር ነው ይላሉ። የቀረው የመዳረሻ መንገድ እንዲሠራም ጠይቀዋል።

በደሴቲቷ ነዋሪ የኾኑት ቄስ ካሳሁን ይስማው ወደቡ ከመገንባቱ በፊት ወደ ቤተ ክርስትያኗ ይመጡ የነበሩት ጎብኝዎች ይቸገሩ እንደነበር አስታውሰዋል። አማኞችም በሌላ ወደብ በመጠቀም እስከ አንድ ሰዓት የሚደርስ የእግር ጉዞ ተጉዘው ይመጡ እንደነበር አንስተዋል።

አሁን ላይ ወደቡ በመገንባቱ ለነዋሪዎቹ እፎይታ እንደፈጠረላቸው ነው የገለጹት። ከወደቡ እስከ ቤተ ክርስትያኗ ያለው የመዳረሻ መንገድ አሁንም ምቹ አለመኾኑን ጠቅሰው በቀጣይ መንገዱ እንዲሠራም ጠይቀዋል።

በዚሁ ጉዳይ ምላሽ የሰጡት አቶ መልካሙ የመዳረሻ ልማት ሥራ በአንድ ጊዜ ተሠርቶ የሚጠናቀቅ ባለመኾኑ በነዋሪዎች የተነሳው ተጨማሪ የመዳረሻ መንገድ ልማት ጥያቄ በቀጣይ ኅብረተሰቡን በማሳተፍ ለማሟላት ጥረት ይደረጋል ነው ያሉት።

ዘጋቢ፦ አሰፋ ልጥገበው

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን

Previous articleየኢትዮጵያ ቡና የራሱን መለያ ይዞ ወደ ዓለም ገበያ እንዲገባ ምን እየተሠራ ነው?
Next articleታላቁ የኢትዮጵያ የሕዳሴ ግድብ የኢትዮጵያውያን ዳግማዊ ዓድዋ