
ባሕር ዳር: ነሐሴ 28/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የገቢ ምንጫችን ቡና ቡና
የኢኮኖሚ ዋልታ ቡና ቡና
ዕውቅ ነው ቡናችን
ቡና ቡና……..ይህ የግጥም ስንኝ በዜማ እና በጥሩ ድምጾች ታሽቶ ረጅም ዓመታት በኢትዮጵያ ሚዲያዎች አስተጋብቷል። እርግጥ ነው ቡና በሀገር ውስጥም ኾነ ከሀገር ውጭ ተቀባይነቱ ከፍ ብሎ የሚታይ ምርትም ነው።
በተለይም እንደ ኢትዮጵያ በእያንዳንዱ ቤት ሰዎችን አሰባስቦ ለውይይት የሚጋብዝ አሰባሳቢ በመኾንም ይታወቃል። ብዙ ጊዜ ኢትዮጵያዊያን የትኩስ ነገር ግብዣ ሲገባበዙም የዚህን ምርት ስም የኾነውን ቡና ሲጠሩ ይሰማል።
ቡና እንዴት እንደተገኘ የቡና እና ሻይ ባለሥልጣን ባሰፈረው ሃሳብ ቡና በመጀመሪያ ጊዜ የታወቀው በኢትዮጵያ እረኞች በ800 ዓ.ም አካባቢ እንደኾነ አትቷል። እንደ መረጃው ከኾነ እረኞቹ ያስተዋሉት ፍየሎቻቸው ቡናውን በልተው ያሳዩት የነበሩት እንቅስቃሴ መሠረት አድርገው እንደኾነም ይገልጻል።
እንደ መረጃው ከኾነ ቡና በምድር ላይ በብዛት ከሚሸጡ ነገሮች ሁለተኛውን ደረጃ የሚይዝ ሲኾን ከ50 በሚበልጡ ሀገራት ገበሬዎች ይመረታል።
የቡና ዘር ሁለት አይነት ሲኾን አረቢያን እና ሮቡስታ በሚልም ነው የሚታወቀው። ኢትዮጵያ በቡና ምርት ደረጃ ከብራዚል፣ ከኮሎምቢያ እና ቬትናም ቀጥላ የምትታወቅ ሀገር ናት።
በኢትዮጵያ አዕምሯዊ ንብረት ባለሥልጣን የሕዝብ ግንኙነት እና ኮሙዩኒኬሽን ሥራ አሥፈጻሚ ብሩክ ወርቅነህ እንደነገሩን ቡናን በርካታ ሀገራት ቢያመርቱትም የኢትዮጵያን ቡና በልዩ ጣዕሙ የራሱን መለያ ይዞ ወደ ገበያ እንዲገባ በአዕምሯዊ ንብረት ለማስመዝገብ ጥረት ተደርጓል።
ኢትዮጵያ የምታመርታቸውን የቡና ምርቶች ተቀባይነታቸው እንዲጨምር እና ልዩ መለያ እንዲኖራቸው ለማድረግ በቻይና እና መሠል ሀገራት መሥራት እንደተቻለ ነው የጠቆሙት።
ሀገሪቱ በተለይም የቡና ምርቷ ዕውቅና እንዲሰጠው ለማድረግ ባለ ልዩ ጣዕም ቡና በሚል ሢሠራ እንደቆየ እና የሲዳሞ ቡና በአዕምሯዊ ንብረትነት በቻይና እንዲመዘገብ ማድረግ ስለመቻሉም ጠቁመዋል።
በተለያየ የሀገሪቱ አካባቢ የተለያዩ ጣዕም ያላቸው የቡና አይነቶች ስላሉም እነዚህን ለማስመዝገብ በትጋት እየተሠራ እንደሚገኝም ነው የጠቆሙት። ሥራ አሥፈጻሚው ሀገሪቱ ከአዕምሯዊ ንብረት ጥበቃ ጋር በተገናኘ የሀገሪቱን ሃብቶች ማስመዝገብ እንዲቻል ሁለት ዓለማቀፍዊ ስምምነቶችን መፈራረሟን ገልጸዋል።
አንደኛው የፓሪስ ኢንዱስትሪያዊ የአዕምሯዊ ንብረት ስምምነት እና የማድሪድ የንግድ ምልክቶች ምዝገባ የአዕምሯዊ ንብረት ስምምነትን በመፈረም የዜጎቿን መብት በዓለም መድረክ ላይ ለማስጠበቅ ትልቅ ጥረት እያደረገች እንደኾነም አስገንዝበዋል።
ሥራ አሥፈጻሚው ይህ ስምምነት ዜጎች በዓለም መድረክ ላይ የአዕምሮ ውጤታቸው በሌሎች እንዳይወሰድ እና ሀገሪቱ በዓለም መድረክ ባሉ ገበያዎች ተወዳዳሪ እንድትኾን የሚያስችሉ በመኾናቸው የተሻለ ሥራ ተሠርቷል ነው ያሉት።
ኢትዮጵያ በቀጣይ ዓመት የዓለም የንግድ ድርጅት ውስጥ ለመግባት እየተንደረደረች በመኾኑ እና ለዚህም የአዕምሯዊ ንብረት ዓለማቀፍ ስምምነትን የሚጠይቅ በመኾኑ እነዚህ ስምምነቶች ጥሩ አቅም እንደሚኾኑ ነው የጠቆሙት።
ቀደም ሲልም የማራካሽ ስምምነቶች በመፈራረም መንግሥት ዓለም አቀፉ መድረክ ላይ በስፋት ለመሳተፍ ጥረት እያደረገ እንደሚገኝም ጠቁመዋል።
ሥራ አሥፈጻሚው ብሩክ ወርቅነህ ቀደም ሲል አርቆ ባለማሰብ እና በተለያዩ ምክንያቶች ከእጅ የወጡ የአዕምሯዊ ንብረቶች ላይ ትምህርት ተወስዶ አሁን ላይ የአዕምሯዊ ንብረትን እንዴት መያዝ እንደሚገባ ማጤን ይገባል ነው ያሉት።
ማንኛውም የፈጠራ ሥራ ጊዜ ሳይሰጠው በአዕምሯዊ ንብረት ቢመዘገብ ለሀገር የሚኖረው ጥቅም ከፍ ያለ በመኾኑ ትኩረት እንዲሰጠውም አሳስበዋል።
ዘጋቢ፦ ምሥጋናው ብርሃኔ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን