
በተፈጠረው ሰላም ባለፉት ዓመታት ሳይታረስ የቆየ ማሳን በዘር መሸፈን ተችሏል።
ደብረ ብርሃን፡ ነሐሴ 28/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በተደጋጋሚ የተፈጠሩ የሕዝብ ለሕዝብ የሰላም መድረኮች ውጤታማ ፍሬ እንዳፈሩ የኤፍራታ እና ግድም ወረዳ አርሶ አደሮች ተናግረዋል።
አቶ ከበደ ግምአለ የላይኛው አጣዬ ቀበሌ አርሶ አደር ናቸው። ከዚህ ቀደም በአካባቢው ተደጋጋሚ ግጭቶች ይከሰቱ እንደነበር ገልጸዋል።
በሰላም እጦቱ ምክንያት ተረጋግተው የግብርና ሥራቸውን ለመከወን ይቸገሩ እንደነበርም ተናግረዋል። በዚህም በርካታ ማሳ ሳይታረስ ቆይቷል ነው ያሉት፡፡
አሁን ላይ ከአጎራባች የኦሮሞ ብሔረሰብ አሥተዳደር ወረዳ እና ቀበሌ ነዋሪዎች ጋር በተፈጠሩ የሕዝብ ለሕዝብ መድረኮች በቀጣናው ሰላም እና መረጋጋትን መፍጠር በመቻሉ ተረጋግተው የግብርና ሥራቸውን እየከወኑ እንደሚገኙ ነው የገለጹት።
በተመሳሳይ አርሶ አደር ሠይድ አልዩ የጀውኃ ቀበሌ ነዋሪ ሲኾኑ አሁን ላይ አካባቢያቸው ሰላም በመኾኑ ሳይታረስ የቀረ ማሳ የለም ብለዋል፡፡
የኤፍራታ እና ግድም ወረዳ ግብርና ጽሕፈት ቤት ኀላፊ እጅጉ ምንከፌ በሰላም እጦት ምክንያት ባለፉት ዓመታት 1 ሺህ 471 ሄክታር መሬት ሳይታረስ መቆየቱን ገልጸዋል።
አሁን ላይ በቀጣናው በተገኘው ሰላም ምክንያት ሳይታረስ ከቆየው መሬት ውስጥ 1 ሺህ 372 ሄክታሩን ማረስ ተችሏል ብለዋል፡፡ ከታረሰው ውስጥም 986 ሄክታሩን በዘር መሸፈን ስለመቻሉም ኀላፊው ገልጸዋል።
የወረዳው ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት የፖለቲካ ዘርፍ ኀላፊ ወንድሙ ካሣ በወረዳው ከሚገኙ 27 ቀበሌዎች ውስጥ 19 ቀበሌዎች ከኦሮሞ ብሔረሰብ አሥተዳደር ቀበሌዎች ጋር እንደሚዋሰኑ ገልጸው የአካባቢው ማኅበረሰብ ከዚሁ አካባቢ ጋር የተዋለደ እና በአብሮነት የተሳሰረ ነው ብለዋል።
ስለኾነም በቀጣናው ሰላም እና መረጋጋት እንዳይኖር የሚሠሩ ኃይሎችን በጋራ ነጥሎ ማውጣት በመቻሉ አካባቢውን ወደ ቀደመ ሰላማዊ ገጽታው መመለስ ተችሏል ነው ያሉት።
የወረዳው አሥተዳደር ሳይታረሱ የቆዩ ማሳዎችን በዘር ለመሸፈን እና በምግብ ዋስትና ራስን ለመቻል ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ እንደሚገኝም አብራርተዋል።
ለዚሁ ሥራም ከ1 ነጥብ 7 ሚሊዮን ብር በላይ በጀት መድቦ ለተግባሩ ልዩ ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ ስለመኾኑም አቶ ወንድሙ ገልጸዋል።
በኤፍራታ እና ግድም ወረዳ አሥተዳደር በ2017/18 የመኽር የምርት ዘመን ከ19 ሺህ ሄክታር በላይ ማሳ በዘር ተሸፍኗል። 709 ሺህ 702 ኩንታል ምርት ለማምረት መታቀዱንም የወረዳው ግብርና ጽሕፈት ቤት መረጃ ያመለክታል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን