
የህጻን ሰሚራ ሕልም ተሳክቷል።
ባሕር ዳር፡ ነሐሴ 28/2017 ዓ.ም (አሚኮ) አቶ ኢብራሂም አደም በደቡብ ወሎ ዞን ከለላ ከተማ የ01 ቀበሌ ነዋሪ ናቸው። እንደ ማንኛውም ነዋሪ ልጅ ወልደው ለማሳደግ እና ለቁምነገር ለማብቃት ሲለፉ ኖረዋል።
በግብርና ሥራ፤ በኋላም በመንግሥት መሥሪያ ቤት ተቀጥረው ሕይወትን ልጅ በማሳደግ እየገፉ ነው።
ልጆቻቸው ዕውቀትን ከሥነ ምግባር ጋር አጣምረው ተምረው ለራሳቸው እና ለወገኖቻቸው ይተርፉ ዘንድ ትምህርት እንዳቅማቸው ያስተምራሉ።
በዕድሜያቸው አመሻሽ የወለዷት የትናንቷ ሕጻን የዛሬዋ ወጣት ሰሚራ ኢብራሂም በታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ሥራ ላይ ያሳረፈችውን አሻራ መለስ ብለን ልናስቃኛችሁ ወደድን።
ሰሚራ ኢብራሂም በ2007 ዓ.ም በሰባት ዓመቷ አንደኛ ክፍል በገባችበት ዓመት ለታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ማስፈጸሚያ ገንዘብ የሚሠበሠብበት ወቅት ነበር።
ሁሉም ኅብረተሰብ በተቻለው አቅም ድጋፉን ለማድረግ ይረባረባል። ተማሪዎች ሳይቀር ገንዘብ ከወላጆቻቸው ተቀብለው ቦንድ ይገዛሉ፤ ይለግሳሉ።
እነ ህጻን ሰሚራም በትምህርት ቤታቸው፣ በሠፈሩ እና በቤተሰቡ ስለ ሕዳሴው ግድብ በጋለ ስሜት ውይይት ሲደረግ ይከታተላሉ። መዝሙር ይዘመራል፣ ስንኝ ይቋጠራል፣ ይፎከራል፣ ቃል ይገባል፤ ገንዘብ ይዋጣል፤ ድጋፍ ይደረጋል።
”ትውልድ እንደ ዥረት የተቀባበለው
ቁጭት ጸጸት ስጋት ሀይ ባይ ሊያገኝ ነው” እና ሌሎችም ቁጭት ፈጣሪ እና ወኔ ቀስቃሽ እና ተስፋ የሚዘሩ መዝሙሮች በሬድዮ፣ በቴሌቪዥን በሻይ ቤቶች እንዲሁም በሆቴሎች ይደመጣሉ። ሁሉም ”በዓባይ ግድብ” እና በሀገር ፍቅር ስሜት አብዷል።
በዛኔዋ ሕጻን ሰሚራ አዕምሮ ውስጥም የወላጅ አባቷ የሀገር ፍቅር ምክር እና የወቅቱ የሕዝቡ ስሜት አንዳች መነሳሳትን ፈጥሯል።
በትምህርት ቤት መዝሙሩ ሲዘመር እና ሲቀሰቀስ ሰምታ ምን ማድረግ እንደሚቻል ጠየቀች። አቅሟ እንደፈቀደ ቦንድ መግዛት መኾኑን ተነገራት።
ሰሚራ ሕጻን ስለኾነች ለታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የምትሰጠው ገንዘብ የላትም። ግን ደግሞ ለግድቡ ገንዘብ ማዋጣት እንደሚገባ ከጓደኞቿ ጋር ተነጋግራለች።
“አባቴ ስለሀገር ፍቅር፤ ለሀገር ምን መኾን እንደሚገባ ይነግረኝ ነበር። እኔም በልቤ የሀገር ፍቅር ስላለኝ ሀገርን ለማሳደግ ጥረት አደርጋለሁ” ያለችው ሰሚራ ለሀገሯ ባላት ምኞት ቦንድ የምትገዛበትን ዕድል አሰላሰለች።
ሃሳቧን ትተገብር ታሪኳን ትሠራ ዘንድም ነገሮች ተገጣጠሙ። የከለላ ከተማ ሕዝብ ለታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ አስተዋጽኦ የሚያደርግበት ውይይት እና የገንዘብ መሠብሠቢያ መድረክ ተዘጋጀ።
“ከቤተሰቦቼ እየተቀበልኩ አጠራቅሜ ከማረባቸው ሦስት ዶሮዎች መካከል አንዱን የመስጠት ሃሳብ መጣልኝ፤ ይህንንም ለወላጆቼ ስነግራቸው ሃሳቤን በደስታ እና በአግራሞት ደገፉልኝ” ትላለች የትናንቷ ሕጻን የዛሬዋ ወጣት ሰሚራ።
ዶሮውንም ለታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የድጋፍ ገንዘብ ወደ ሚሠበሠብበት ወስዳ አቀረበች። ሕዝቡም በደስታ ተቀብሎ ዶሮውን ለጨረታ ማቅረቡን ነግራናለች። እሷም ባደረገችው ነገር መደሰቷን አስታውሳለች።
በጨረታው ዶሮው 17 ሺህ ብር ተሽጦ ቦንድ እንደተገዛላት ሰሚራ ገልጻለች። ሌሎች ተማሪዎችም ታሪኳን ሰምተው በመነሳሳት እንደ ሰሚራ ቦንድ ግዙልን እያሉ ቤተሰቦቻቸውን በመጠየቅ ለታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ አስተዋፅኦ ማበርከታቸውን ገልጻለች።
አሁን በሳዑዲ አረቢያ የምትኖረው ሰሚራ ለአሚኮ በሰጠችው አስተያየት አሻራዋ ያለበት የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ አልቆ ሊመረቅ እንደኾነ ስትሰማ መደሰቷን ነግራናለች።
የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ መጠናቀቅ የሁላችንም ርብርብ እና አሻራ ነው ያለችው ወጣት ሰሚራ ለሀገሯ ከዚህም በላይ እንድታድግ ፍላጎቷ እና ምኞቷ መኾኑን ገልጻለች።
ለወደፊትም ለሀገሯ ሌላ አስተዋጽኦ ለማበርከት ፍላጎቱ እንዳላት ተናግራለች።
ለሀገር መሥራት እና መስዋዕት የመኾንን አስፈላጊነት የጠቀሰችው ሰሚራ ሀገርን ትልቅ ደረጃ ለማድረስ ትንሽ ትልቅ እንደማይለይም አንስታለች። ሀገር ከዚህ በላይ እንድታድግ በገንዘብም በዕውቀትም መርዳት እንደሚያስፈልግ መክራለች።
ዛሬ ላይ በሕይወት የሌሉት አባቷ ትምህርቷን አጠናቃ በዕውቀት እና በሥነ ምግባር የታነጸች እንድትኾንላቸው ይመክሯት እንደነበር ወጣት ሰሚራ ገልጻለች።
ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ተጠናቅቆ ለምርቃት በመብቃቱ የተደሰተችው ሰሚራ ”ብችል በግድቡ ምርቃት ተገኝቼ መጎብኘት እፈልግ ነበር” ብላለች።
ዘጋቢ፦ ዋሴ ባዬ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን