“ግጭት እና ፖለቲካ ከትምህርት ቤቶች ይራቅ” የአማራ ክልል የተማሪ ወላጆች ማኅበር

9

“ግጭት እና ፖለቲካ ከትምህርት ቤቶች ይራቅ” የአማራ ክልል የተማሪ ወላጆች ማኅበር

ባሕር ዳር: ነሐሴ 28/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ትምህርት ቤቶች ዋና ዓላማቸው ትውልድን መቅረጽ ነው። የሀገር እና የሕዝብን የማደግ ሕልም እና ትልም ተቀብሎ በብቃት ሊፈጽም የሚችል ትውልድ መገንባት በትምህርት ቤቶች ላይ የተጣለ አደራ ነው።

ይህንን ከባድ አደራ ተሸክመው የሚታትሩ ትምህርት ቤቶችን መደገፍ እና ተግባራቸውን ማሳለጥ ደግሞ የሁሉም ዜጎች ኀላፊነት ነው።

በአማራ ክልል በተደጋጋሚ የሚከሰተው ግጭት በክልሉ ትምህርት ቤቶች እና በትምህርት ላይ የከፋ ችግር ደቅኖ ቆይቷል። ሕጻናት ፊደል መቁጠር በሚገባቸው የዕድሜ ክልል ሳይጠቀሙበት ቤት ተቀምጠው ከርመዋል። ወጣቶች መገኘት በሌለባቸው ቦታዎች ላይ ውለዋል።

በተለይም በገጠራማው የክልሉ አካባቢዎች የሚገኙ ሴቶች ያለዕድሜያቸው ወደ ጋብቻ ገብተው ሩቅ ሕልማቸው ቅርብ አድሯል። ወደየከተሞች እየገቡ በቤት ሠራተኝነት በመሠማራት የዕውቀት ጊዜያቸውን የሚያባክኑት በርካቶች እንደኾኑ የአደባባይ ሃቅ ኾኗል።

የአማራ ክልል የተማሪ ወላጆች ኅብረት ፕሬዝዳንት አዱኛ እሸቴ “በልጆቻችን ትምህርት እና ሕይዎት ላይ የተደቀነው አደጋ ከዚህ በላይ መቀጠል የለበትም፤ በጋራ ቆመን ይበቃል ልንለው ይገባል” ብለዋል።

ትምህርት ቤቶች እየወደሙ እና ተማሪዎች ከትምህርት ገበታቸው እየታገዱ የምንገነባት ሀገር ለማንም አትመችም፤ ይልቁንም በድህነት አዙሪት የተተበተበች እና ድህነቱ በሚወልደው ግጭት የምትታመስ ትኾናለች ነው ያሉት።

ማንም ቢኾን ይህንን በውል በመገንዘብ ትምህርት ቤቶችን ያለምንም ቅድመ ሁኔታ መክፈት እና ተማሪዎች እንዲማሩ መፍቀድ አለበት ሲሉም አባታዊ ምክራቸውን አስተላልፈዋል።

በየትምህርት ቤቶች የተዋቀረ የወላጅ እና መምህራን ኅብረት መኖሩን የገለጹት ፕሬዚዳንቱ ኅብረቶች ተማሪዎችን ወደ ትምህርት ቤት ለመመለስ በትኩረት ሊሠሩ እንደሚገባም መልእክት አስተላልፈዋል።

የአማራ ክልል የተማሪ ወላጆች ኅብረት ከየትኛውም ዓይነት ፖለቲካ ገለልተኛ በመኾን ለልጆች ትምህርት መቃናት ብቻ እንደሚሠራም ፕሬዝዳንቱ ገልጸዋል።

“ታጥቀው በጫካ ያሉ ወጣቶችም የኛው ልጆች ናቸው፤ ሰላም ወርዶ መልካም ኑሮን እንዲኖሩ እንፈልጋለን፤ እነዚህ ታጣቂዎች የተማሪዎችን የከፋ አዋዋል በውል ተገንዝበው ለትምህርት ቤቶች መከፈት አስፈላጊውን ሁሉ ድጋፍ ማድረግ እንጅ ማደናቀፍ ማብቃት አለበት” ብለዋል።

ኢትዮጵያ ሁላችንም የኔ የምንላት ሀገር ናት፤ ነገን ልትሻገር የምትችለው የተማረ ትውልድ ሲኖር ነው፤ ማንም ቢኾን ትምህርትን ማስተጓጎል የለበትም ነው ያሉት።

“ትምህርት ቤቶችን መዝጋት የፖለቲካ ትርፍ አያስገኝም፤ የትኛውም ዓይነት “ግጭት እና ፖለቲካ ከትምህርት ቤቶች መራቅ አለበት”፤ ተማሪዎችም ከየትኛውም ጫና ነጻ ኾነው መማር እና መወዳደር አለባቸው ብለዋል አቶ አዱኛ።

ያሳለፍነው የትምህርት ሥብራት ይበቃል፤ የፈረሱ ትምህርት ቤቶችን ለመጠገን፣ ከትምህርት ርቀው የቆዩ ልጆችን በሥነ ልቦና ለመደገፍ፣ በቀጣይም ያለማቋረጥ እንዲማሩ በጋራ መሥራት ይገባል ነው ያሉት።

በተለይም የተማሪ ወላጆች ልጆቻቸውን በወቅቱ በማስመዝገብ ወደ ትምህርት ቤት ለመላክ መበርታት እንዳለባቸው ፕሬዝዳንቱ መልዕክት አስተላልፈዋል።

ከዚህ በፊትም መስዕዋትነት እየከፈሉ የልጆቻቸው ትምህርት እንዳይቋረጥ ያደረጉ ወላጆች መኖራቸውን ጠቅሰው ይህ ተግባር ከልጆቻቸውም በላይ ለሀገርም ትልቅ ውለታ ነው ብለዋል።

በመንግሥት በኩልም አስፈላጊው የትምህርት ቁሳቁስ እንዲሟላ ጠይቀዋል። ዋጋ እየከፈሉ ጭምር ሲያስተምሩ የቆዩ መምህራን እንዳሉ ጠቅሰው ያመሰገኑት አቶ አዱኛ አሁንም ቢኾን በየትምህርት ቤቶች በወቅቱ በመገኘት የዕውቀት አባትነት ሚናቸውን እንዲወጡ ጠይቀዋል።

“ያልተማረ ትውልድ ሊኖረን አይገባም፤ ወደምናልመው ለውጥ እና እድገት ሁሉ አያሻግረንምና” ያሉት ፕሬዝዳንቱ በትምህርት ጉዳይ ሁሉም በጋራ ቆሞ በመምከር እና ትምህርት ቤቶች መከፈት አለበባቸው ነው ያሉት።

ያለፈው ሊቆጨን ይገባል፤ ጥፋትን መድገምም የለብንም፤ የተከፈቱ ትምህርት ቤቶች እና በዕውቀት ገበታቸው ላይ የሚውሉ ልጆችን ብቻ ማየት እንሻለን ሲሉም አባታዊ አደራቸውን አስተላልፈዋል።

2018 የትምህርት ዘመን ሁሉም ተማሪዎች ወደ ትምህርት ቤት ተመልሰው በሰላም የሚማሩበት፤ ለልጆቻቸው አዋዋል የሚጨነቁ ወላጆችም እፎይታን የሚያገኙበት የዕውቀት ዓመት እንዲኾንም ተመኝተዋል።

ዘጋቢ፦ አሚናዳብ አራጋው

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየኢትዮጵያን ምርት በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ ለማድረግ መንግሥት ለጥራት ትኩረት ስጥቶ እየሠራ ነው። 
Next articleየህጻን ሰሚራ ሕልም ተሳክቷል።