
አዲስ አበባ፡ ነሐሴ 27/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በወጭ ምርት ጥራት ላይ ያተኮረ የፓናል ውይይት በጥራት መንደር እየተካሄደ ነው።
የንግድ እና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ካሳሁን ጎፌ (ዶ.ር) ማምረት በራሱ በቂ ባለመኾኑ እና ጥራት የንግድ ልብ መኾኑን በመገንዘብ ምርቱ ተፈላጊ እንዲኾን መሥራት ይገባል ብለዋል።
መንግሥት ለጥራት ቅድሚያ በመስጠት በ8 ቢሊዮን ብር ወጭ የጥራት መንደር ገንብቷል ነው ያሉት።
የጥራት መንደሩ በርካታ ጥራትን የሚያረጋግጡ ላብራቶሪዎች እና ብቁ የሰው ኃይሎችን በማሟላት ወደ ሥራ መግባቱንም ገልጸዋል።
ይሁን እንጂ ይሄ በቂ ባለመኾኑ አስገዳጅ የኾኑ እና ያልኾኑ የጥራት ደረጃዎችን በማውጣት የኢትዮጵያ ምርት በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ የሚያደርግ መስፈርት ወጥቶ እየተሠራ መኾኑንም ሚኒስትሩ አብራርተዋል።
ኢትዮጵያ በ2017 በጀት ዓመት ከወጭ ንግድ 8 ነጥብ 3 ቢሊዮን ዶላር ማግኘቷን የገለጹት ዶክተር ካሳሁን በ2018 በጀት ዓመት ለማግኘት ለታቀደው 9 ነጥብ 4 ቢሊዮን ዶላር የወጭ ንግድ ገቢ ጥራት ላይ ትኩረት አድርጎ መሥራት ይገባል ብለዋል።
በመድረኩ የምርት እና የአገልግሎት ጥራት ላይ ያተኮረ የፓናል ውይይት የተደረገ ሲኾን የጥራት መሠረተ ልማት ለሀገር ዕድገት ያለው ፋይዳን በተመለከተም ዘጋቢ ፊልም ቀርቧል።
ዘጋቢ፦ ቤተልሄም ሰለሞን
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን