የወልቃይት ጠገዴን ሕዝብ የወሰን እና ማንነት ጥያቄ ሕጋዊ ምላሽ እንዲያገኝ በሚደረገው ጥረት የወጣቶች ሚና ከፍተኛ ነው።

21
ሁመራ፡ ነሐሴ 27/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ለውጥ እና ነጻነት እንዲመጣ መስዋዕትነት ሲከፍሉ የነበሩ ወጣቶች ዛሬ ላይ የሕዝቡ ማንነት እና ወሰን እንዲረጋገጥ እየሠሩ መኾኑን የወልቃይት ጠገዴ አማራ ማንነት እና ወሰን አስመላሽ ኮሚቴ ገልጿል።
ወጣቶች የማንነት እና ወሰን ጥያቄው እንዲረጋገጥ ከዞን እስከ ቀበሌ በተዘረጉ አደረጃጀቶች እየሠሩ መኾኑም ተገልጿል።
የወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ሕዝብ ከህወሓት የጭቆና አገዛዝ ነጻ ለመውጣት በተደረገው እልህ አስጨራሽ ትግል መስዋዕትነትን ከፍሏል፡፡
የአካባቢው ወጣቶችም ለዘመናት ተጭኗቸው ከነበረው ጭቆና ለመላቀቅ ከውስጥ እና ከውጭ ኾነው መራራ መስዋዕትነትን ከፍለው አካባቢያቸውን ነጻ ካወጡ ዓመታት ተቆጥረዋል።
ትናንት ለውጥ እና ነጻነት እንዲመጣ መስዋዕትነት ሲከፍሉ የነበሩ ወጣቶች የአማራነት ማንነት ጥያቄያቸው እንዲረጋገጥ እየሠሩ መኾኑንም የወሰን እና ማንነት አስመላሽ ኮሚቴው ንዑስ አባል ወጣት ታዴ ነጋሽ ለአሚኮ ተናግሯል።
ወጣት ታዴ “እኛ ወደ መሪነት የመጣነው ትናንት በተከፈለው መራር መስዋእትነት ነው” ብሏል።
ትግሉ በቅብብል እየተመራ መኾኑን የጠቀሰው ወጣት ታዴ በዚህም ወጣቶች የለውጡ መሪ እየኾኑ ነው ብሏል።
የማንነት እና ወሰን የማስከበር ትግሉ ግቡን እንዲመታ ለወጣቶች ኀላፊነት ተሰጥቶ እየተሠራ መኾኑን ሌላኛው የኮሚቴው ንዑስ አባል ወጣት ጌታቸው ደሳለኝ ተናግሯል።
ከዚህ በፊት የነበረው ኮሚቴ “አስመላሽ” እንደነበር የጠቆመው ወጣት ጌታቸው ዛሬ ወጣቱ ትግሉን ፈጻሚ እንዲኾን እየተሠራ መኾኑንም አስረድቷል።
አስመላሽ ኮሚቴው የማንነት እና ወሰን ጥያቄዎችን ከሞላ ጎደል ማስመለሱን ያነሳው ወጣት ጌታቸው ወጣቱ ትግሉን ለማስፈጸም ኀላፊነት የተጣለበት መኾኑን ጠቅሷል።
በሕዝብ የተመረጡ እና የሕዝቡን ጥያቄ ዳር የሚያደርሱ ወጣቶች በኮሚቴው ውስጥ መካተታቸውን የወሰን እና ማንነት አስመላሽ ኮሚቴው ምክትል ሠብሣቢ ጌጤ አዳል አስረድተዋል።
በትግሉ ውስጥ ወጣቱ በውስጥ እና በውጭ ኾኖ መስዋዕትነት ይከፍል ነበር ብለዋል። ይሄንን ወጣት ወደ ኀላፊነት በማምጣት ትግሉን እንዲመራ ማድረግ ለሚኖረው ውጤት አይነተኛ መፍትሄ መኾኑንም ነው አቶ ጌጤ የተናገሩት።
የወልቃይት ጠገዴ ሕዝብ አማራዊ ማንነት በሕግ አግባብ እንዲፈታ ወጣቶች የድርሻቸውን እንዲወጡም ጥሪ ቀርቧል፡፡
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን
Previous articleትምህርት ትውልድን ማስቀጠል በመኾኑ የትኛውም አካል በትምህርት ጉዳይ ዝም ሊል አይገባም። 
Next article“ጳጉሜ 1 የጽናት ቀን በሚል ይከበራል” ለገሠ ቱሉ (ዶ.ር)