
ፍኖተ ሰላም: ነሐሴ 27/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ተማሪ ዮሴፍ ወርቁ እና ተማሪ መሠረት ካሳሁን በፍኖተ ሰላም ከተማ ባከል የአንደኛ እና የመካከለኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የ7ኛ እና 8ኛ ክፍል ተማሪዎች ናቸው። ተማሪዎቹን ለ2018 የትምህርት ዘመን ሲመዘገቡ ነው አሚኮ ያገኛቸው።
ተማሪዎቹ በሰጡት ሃሳብ በ2016 ዓ.ም ሙሉ ለሙሉ ትምህርት ተቋርጦ ስለነበር ለሥነ ልቦና ቀውስ ተዳርገው እንደነበር ያስታውሳሉ።
በ2017 የትምህርት ዘመን መማር ማስተማር ዘግይቶ ቢጀመርም ግጭት በሚከሰትበት ጊዜ ትምህርቱ በመቆራረጡ ተረጋግተው መማር አለመቻላቸውን ይናገራሉ።
በዚሁ ምክንያት ወደ ትምህርት ቤት መምጣት ያቋረጡ ተማሪዎች ብዙዎች መኾናቸውን ገልጸዋል። በዚህ ዓመት ግን ቀድመው በመመዝገባቸው የትምህርት ዘመን ተስፋቸውን እንዳለመለመው ተናግረዋል።
መማር ማስተማሩ በተሳካ ሁኔታ እንዲቀጥልም ያላቸውን መልካም ምኞት ገልጸዋል። ለዚህም ሁሉም እገዛ እንዲያደርግላቸው ነው የጠየቁት።
የፍኖተ ሰላም ከተማ አሥተዳደር ትምህርት ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ደረጀ ታደሰ በ2018 የትምህርት ዘመን ከ23 ሺህ 696 በላይ ተማሪዎችን በመመዝገብ ለማስተማር እየተሠራ መኾኑን ተናግረዋል።
እሰካሁንም 3 ሺህ 242 ተማሪዎች መመዝገባቸውን ኀላፊው ገልጸዋል።
ባለፉት ሁለት ዓመታት በምዕራብ ጎጃም ዞን ከ360 ሺህ በላይ ተማሪዎች ከትምህርት ገበታ ርቀው መቆታቸውን የዞኑ ትምህርት መምሪያ ምክል ኀላፊ መኩሪያው ገረመው ተናግረዋል።
በዚህም በርካታ ተማሪዎች ለያለዕድሜ ጋብቻ፣ ለሥነ ልቦና ቀውስ እና ለተለያዩ ችግሮች ተጋላጭ ኹነዋል ብለዋል።
በ2018 የትምህርት ዘመን 426 ሺህ 29 ተማሪዎችን መዝግቦ ለማስተማር ርብርብ እየተደረገ መኾኑንም ነው የገለጹት።
ተማሪዎችን ማስተማር ትውልድን ማስቀጠል በመኾኑ የትኛውም አካል በትምህርት ጉዳይ ዝም ሊል አይገባም ነው ያሉት።
በተለይም ትምህርትን ከፖለቲካ ወገንተኝነት ነጻ በማድረግ ተማሪዎች ወደ ትምህርት ገበታቸው እንዲመለሱ ሁሉም የበኩሉን እንዲወጣ ጠይቀዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን