
ባሕር ዳር: ነሐሴ 27/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የግብር ሥርዓት ግብር ከፋዮች ለመንግሥት ክፍያ የሚፈጽሙበት ሥርዓት ነው። ግብር ዋናው የመንግሥት የፋይናንስ ምንጭም ነው። ለአንድ ሀገር የኢኮኖሚ ልማት እና እድገት የጀርባ አጥንት ነው ማለትም ይቻላል። መንግሥት አስተማማኝ የገቢ ምንጭ የሚያገኘውም ከግለሰቦች እና ከድርጅቶች በሚሰበሰብ የግብር ገቢ ነው፡፡
መንግሥት ደግሞ በምትኩ በቀጥታም ኾነ በተዘዋዋሪ ለሕዝቦቹ አገልግሎት ያቀርብበታል፣ መሠረተ ልማቶችንም ያሟላበታል፡፡
የግብር ሥርዓት ከገቢ ምንጭነት ባሻገር በኅብረተሰቡ ዘንድ ፍትሐዊ የሃብት ክፍፍል እንዲኖር ያደርጋል። የኢኮኖሚውን አቅጣጫ ለመምራት፣ ኢንቨስትመንትን ለማበረታታት እንዱሁም ልማትን ለማፋጠን የሚያገለግል የፊዚካል ፖሊሲ መሳሪያ መኾኑንም በባለሙያዎች ይገለጻል፡፡
ግብር የሚጣለው እና የሚሰበሰበው በመንግሥት ብቻ ነው፡፡ ዓላማውም ለጠቅላላው ኅብረተሰብ ጥቅም ሲኾን ግብር ከፋዩ ለከፈለው ግብር ቀጥታ ከመንግሥት በግሉ ልዩ ጥቅም የመጠየቅ መብት እንደሌለውም የገቢ ግብር ሥርዓቱ ያትታል፡፡
ግብር የሚጣልባቸው የገቢ ምንጮች ገቢ የሚያስገኙ የምርት፣ የአገልግሎት እና የንግድ ወይም የሥራ ዘርፍ ሲኾኑ የግብር መጠን ደግሞ በእነዚሁ ገቢዎች ላይ የሚጣለው የግብር መጠን ነው፡፡
ግብር በሕግ የሚጣል የዜጎች ግዴታ ነው። በፍላጎት ሳይኾን በግዳጅ የሚከፈልም ነው፡፡ ይህም ቀድሞ በተደነገገ ሕግ መሠረት የሚፈጸም ነው፡፡ አለመክፈልም በወንጀል ሕግ እና በአሥተዳደር ሕግ ያስጠይቃል፡፡
በአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን የሕግ አገልግሎት ዳይሬክቶሬት ከፋተኛ የሕግ ባለሙያ ደመቀ ይብሬ ከግብር ጋር በተያያዘ በታክስ ከፋዮች የሚፈጸሙ በርካታ የታክስ ወንጀሎች መኖራቸውን ይገልጻሉ፡፡ ከእነዚህም መካከል ግብርን በመክፈያው ጊዜ ውስጥ አለመክፈል እና የግብር ስወራ ወንጀሎች ተጠቃሽ ናቸው ብለዋል፡፡
እንደ ባለሙያው ማብራሪያ እነዚህ የታክስ ወንጀሎች ተፈጽመው ሲገኙ እንደነገሩ ሁኔታ ታይቶ የወንጀል እና አሥተዳደራዊ ተጠያቂነትን ያስከትላሉ ነው ያሉት፡፡ በአማራ ክልል የታክስ አሥተዳደር አዋጅ ቁጥር 241/2008 ላይ የታክስ ግዴታ አለመወጣትን ተከትሎ የሚመጡ ተጠያቂነቶችን በሁለት መልኩ ተደንግገው እንደሚገኙ ነው ያስረዱት፡፡
እነዚህም የወንጀል ተጠያቂነት እና የአሥተዳደራዊ ተጠያቂነት በሚል የተደነገጉ ናቸው፡፡
👉 አሥተዳደራዊ ተጠያቂነት
የታክስ ግዴታውን ባልተወጣ ግብር ከፋይ ላይ በገቢ ሰብሳቢው መሥሪያ ቤት ትዕዛዝ ድርጅቱን እስከ ማሳሸግ የሚደርስ አሥተዳደራዊ እርምጃ እንደሚያስወስድ በአዋጁ አንቀጽ 48 ላይ በግልጽ እንደተቀመጠ አስረድተዋል።
በተጨማሪም በገቢ ሰብሳቢው መሥሪያ ቤት የሚጣል አሥተዳደራዊ የገንዘብ መቀጮ አንዱ የአሥተዳደራዊ ተጠያቂነት አይነት ስለመኾኑም አብራርተዋል፡።
👉የወንጀል ተጠያቂነት
የወንጀል ተጠያቂነቱ ደግሞ የእስራት ወይም የገንዘብ መቀጮ መኾኑንም ጠቁመዋል። በታክስ ላይ የሚፈጸሙ ወንጀሎች የኢትዮጵያን የወንጀል ሕግ በመተላለፍ የሚፈጸሙ በመኾናቸው ክሱ የሚመሠረተው፣ የሚታየው እና የይግባኝ ሥርዓቱ የሚመራው በኢትዮጵያ የወንጀል ሥነ ሥርዓት ሕግ መሠረት ስለመኾኑም አብራርተዋል፡፡
ማንኛውም ግብር ከፋይ በግብር መክፈያ ጊዜው ውስጥ ሳይከፍል ከቀረ ለዘገየበት ጊዜ ተጨማሪ ቅጣት ያስከትላል ነው ያሉት።
👉ለአንድ ወር ወይም የወሩ ከፊል ለኾነው ጊዜ ባልተከፈለው ግብር ላይ 5% (አምስት በመቶ)፣ እንዲሁም ከአንድ ወር በኋላ ለዘገየበት ለእያንዳንዱ ወር ወይም የወሩ ከፊል ለኾነው ጊዜ ባልተከፈለው ግብር ላይ ተጨማሪ 2% (ሁለት በመቶ) ቅጣት እንደሚከፍል በአዋጁ ተደንግጓል፡፡
👉የግብር ስወራ ወንጀል ተጠያቂነትን በተመለከተ
ማንኛውም ሰው ግብርን ለመሰወር በማሰብ ገቢውን የደበቀ ፣የታክስ ማሳወቂያውን ያላቀረበ ወይም ታክሱን ያልከፈለ እንደኾነ ከብር 100 ሺህ እስከ ብር 200 ሺህ ብር በሚደርስ የገንዘብ ቅጣት እና ከሦስት ዓመት እስከ አምስት ዓመት በሚደርስ ጽኑ እስራት ይቀጣል፡፡
ከተከፋይ ሒሳብ ላይ ግብርን ቀንሶ ገቢ የማድረግ ኀላፊነት የተጣለበት ሰው ግብርን ለመሰወር በማሰብ ቀንሶ የያዘውን ታክስ ለባለሥልጣኑ ያላስተላለፈ ከኾነ ከሦስት ዓመት እስከ አምስት ዓመት በሚደርስ ጽኑ እስራት ይቀጣል፡፡
👉የግብር ግዴታን በተመለከተ
የሕግ ባለሙያው አቶ ደመቀ እንዳስረዱት አንድን ድርጊት መፈጸም ወይም አለመፈጸም አሥተዳደራዊ ቅጣት እና የወንጀል ኀላፊነት የሚያስከትል በሚኾንበት ጊዜ ጥፋቱን የፈጸመው ሰው አሥተዳደራዊ መቀጫ መቀጣቱ የወንጀል ተጠያቂነቱን አያስቀርም፡፡
ማንኛውም ታክስ ከፋይ አሥተዳደራዊ ቅጣት የተጣለበት ወይም የወንጀል ክስ የቀረበበት መኾኑ መክፈል የሚገባውን ታክስ የመክፈል ግዴታውን አያስቀርም፡፡
በመኾኑም ግብር ከፋዩ ይህን ሕጋዊ ግዴታ አውቆ መክፈል የሚገባውን ግብር በወቅቱ መክፈል እንደሚኖርበት የሕግ ባለሙያው አስገንዝበዋል፡፡
ግብር ሰብሳቢው መሥሪያ ቤትም ለግብር ከፋዮች ተገቢውን ፍትሐዊ አገልግሎት መስጠት ያለበት ሲኾን ኀላፊነቱን ወደ ጎን በመተው ተገቢ ያልኾነ ጥቅም ለማግኘት ወይም ለማስገኘት በሚሠራ የመሥሪያ ቤቱ አካል ላይ አስፈላጊው እርምጃ መወሰድ እንደሚኖርበትም አመላክተዋል።
ዘጋቢ፦ አሰፋ ልጥገበው
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!