
ባሕር ዳር: ነሐሴ 26/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል የምግብ ሥርዓት እና ሥርዓተ ምግብ ምክር ቤት መክፈቻ እና የ2018 በጀት ዓመት ዕቅድ ትውውቅ እየተካሄደ ነው።
በመክፈቻ ሥነ ሥርዓቱ የአማራ ክልል ምክትል ርእሰ መሥተዳድር አብዱ ሁሴንን (ዶ.ር) ጨምሮ ሌሎች ከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎች ተገኝተዋል።
የአማራ ክልል የምግብ ሥርዓት እና ሥርዓተ ምግብ ምክር ቤት የምግብ እና የሥርዓተ ምግብ ሥራዎችን በትኩረት በመምራት በሰው ጤና፣ በምርታማነት ላይ አሉታዊ ጫና እያሳደሩ ያሉትን ከመቀንጨር፣ ከመቀጨጭ እና ከሥርዓተ ምግብ መዛባት ጋር የተያያዙ ችግሮች እንዲቀረፉ ይሠራል ተብሏል።
በመርሐ ግብሩ ላይ መልዕክት ያስተላለፉት
የርእሰ መሥተዳድሩ የሰቆጣ ቃል ኪዳን አማካሪ ባዘዘው ጫኔ የየትኛውም ሥራ ስኬት መለኪያ በአካል እና በአዕምሮ የበለጸገ ትውልድ መፍጠር ነው ብለዋል።
የምግብ ሥርዓት እና ሥርዓተ ምግብን ማስተካከል ለትውልድ ግንባታ ታላቅ አስተዋጽኦ እንዳለው ተናግረዋል። ብቁ ሀገር ተረካቢ ትውልድ ለመፍጠር ይሄን መሥራት ያስፈልጋል ነው ያሉት።
በክልሉ የመቀንጨር እና የመቀጨጭ ችግሮችን ለመቀነስ በተሠራው ሥራ አበረታች ለውጦች መመዝገባቸውንም ተናግረዋል። ነገር ግን አሁንም መሠረታዊ ችግሮች እንዳሉ ገልጸዋል።
የክልሉን ሥርዓተ ምግብ ለማስተካከል ተጨማሪ ሥራ እንደሚጠይቅም አብራርተዋል። አሁንም የሥርዓተ ምግብ ግንዛቤ ገና ችግር ያለበት ነው ብለዋል። ሀገር ተረካቢ ትውልድ ለመፍጠር የምግብ ሥርዓት እና የሥርዓተ ምግብን በተገቢው መንገድ መምራት ይገባል ነው ያሉት።
የክልሉ መንግሥት የምግብ ሥርዓት እና ሥርዓተ ምግብ ችግርን ለመፍታት እና ብቁ ዜጋ ለመፍጠር የሚያስችል ሥራ ለመሥራት የምግብ ሥርዓት እና ሥርዓተ ምግብ ምክር ቤት ማቋቋሙን ገልጸዋል። ይህም ትልቅ ርምጃ ነው ብለዋል።
የአማራ ክልል ምክትል ርእሰ መሥተዳድር አብዱ ሁሴን (ዶ.ር) የምግብ ሥርዓት እና ሥርዓተ ምግብ ብዙ ጉዳዮችን የያዘ ጽንሰ ሀሳብ መኾኑን ተናግረዋል። ብዙ ጽንሰ ሃሳብ የያዘውን ጉዳይ ለመተግበር የሁሉም ቅንጅት እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል። የምክር ቤቱ መቋቋም ሥራውን በውጤታማነት ለመምራት እንደሚያስችልም ተናግረዋል።
የመቀንጨር እና የመቀጨጭ ችግሮችን ለመቀነስ በተሠራው ሥራ ውጤት መገኘቱን የተናገሩት ምክትል ርእሰ መሥተዳድሩ አሁንም የሁሉንም ርብብር የሚጠይቁ ችግሮች አሉ ነው ያሉት። ሀገር የሚረከብ ብቁ ዜጋ ለመገንባት ምግብ እና ሥርዓተ ምግብ ላይ መሥራት ይጠበቃል ብለዋል። የመቀንጨር እና መቀጨጭ ችግርን ለሕዝብ ክብር ሲባል መፈታት የሚገባው ጉዳይ ነው ብለዋል።
ችግሮችን ለመፍታት ምርት እና ምርታማነትን ማሳደግ፣ የምርት ጥራትን ማበልጸግ እና አጠቃቀሙን ማዘመን ያስፈልጋል ነው ያሉት።
የምግብ ሥርዓት እና ሥርዓተ ምግብን ውጤታማ ለማድረግ በትኩረት መሥራት እንደሚገባም አመላክተዋል።
ዘጋቢ:- ታርቆ ክንዴ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን