
ደብረ ማርቆስ: ነሐሴ 26/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የደብረ ማርቆስ ከተማ የመንግሥት ሠራተኞች ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ለፍፃሜ በመብቃቱ የተሰማቸውን ደስታ ገልጸዋል።
አስተያየት ሰጭዎቹ የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የዘመናት ቁጭት የወለደው፣ የይቻላል ስሜትን የፈጠረ እና ኢትዮጵያውያን በተባበረ ክንድ የትኛውንም ልማት ማሳካት እንደሚችሉ ማሳያ የኾነ ትልቅ ሃብት ነው ብለዋል።
ግድቡ ከኢትዮጵያ አልፎ ለተፋሰሱ ሀገራት እና ለመላው አፍሪካ ትልቅ ተስፋ የሚሰጥ ስለመኾኑም ተናግረዋል።
ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ማኅበራዊ ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ አንደምታው ግዙፍ መኾኑን የተናገሩት አስተያየት ሰጭዎቹ ኢትዮጵያ ለተያያዘችው ድህነትን የመዋጋት እና ከተረጂነት የመውጣት ትግል የማይተካ ሚና ይጫወታል ነው ያሉት።
ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ በርካታ ውጣውረዶችን እና አሻጥሮችን ሰብሮ ለፍፃሜ የደረሰ ፕሮጀክት ነው ያሉት የመንግሥት ሠራተኞቹ የውጤታማ ዲፕሎማሲ ማሳያ፤ የመተባበር እና የአይበገሬነት ተምሳሌት ስለመኾኑም አስረድተዋል።
ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ኢትዮጵያውያን ጀምረው መጨረስ እንደሚችሉ ያሳየ እና እንደ ሀገር ሌሎች ሜጋ ፕሮጀክቶችንም ገንብቶ ለማጠናቀቅ ተምሳሌት እና አዲስ ምዕራፍ የከፈተ ነው ብለዋል አስተያየት ሰጭዎቹ።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን