የኢትዮጵያ ሀገር መከላከያ ሠራዊት ደማቅ አሻራ ያረፈበት ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ።

18
ባሕር ዳር: ነሐሴ 26/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ዓባይ በቤቱ እንዳያድር፤ ለባለቤቱ እንዳይጠቅም፤ ያልተገባ ዕግድ ተጥሎበት ለኢትዮጵያውያን ባዳ ኾኖ ኖሯል። ይህንን ታሪክ ለመቀየር በየዘመኑ ያለፉ የኢትዮጵያ መሪዎች ብርቱ ጥረት አድርገዋል።
መሪዎችም መላው ኢትዮጵያውያንን አስተባብረው ከዓለም ሀገራት ጋር ሞግተዋል። በተለይም የኢትዮጵያን ዕድገት የማይመኙ ኢትዮጵያ ጠል ሀገራት በእጅ አዙር ሕግ አሥረው የራሳቸውን አሉታዊ ጫና ለማሳደር ጥረት ቢያደርጉም በሰላ የዲፕሎማሲ ትግል ሴራውን በጣጥሰውታል።
ዛሬ ዓባይ ተገድቦ የሚሊዮኖች ኢትዮጵያውያን የደስታ ምንጭ ሊኾን እና የድል ብስራት ሊበሰርም እነኾ ጥቂት ቀናት ብቻ ቀርተውታል።
ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የአይኾንም ትርክትን ያስወገደ፣ ባዕዳንን ቅስም የሰበረ፣ የኢትዮጵያን ልዕልና ከፍ ያደረገ፣ የከፍታዋን ጉዞ ያሳየ የዘመኑ ክስተት ኾኗል።
ባለ ደማቅ ታሪክ የኾነችው ኢትዮጵያ አኹንም በኢትዮጵያ የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ሌላ ታሪክ ጽፋለች። ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ሁሉንም ኢትዮጵያውያንን አስተሳስሯል።
በታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ ሂደት ዘመን የማይሽረው ተጋድሎ ካደረጉት እና ደማቅ ታሪክ ከጻፉት አካላት መካከል የኢትዮጵያ የሀገር መከላከያ ሠራዊት በግንባር ቀደምትነት ይጠቀሳል።
የሀገር መከላከያ ሠራዊት ለኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ እውን መኾን ሁሉንም ሰጥቷል። ገንዘብ አዋጥቷል፣ በጉልበት ደግፏል፣ እስከ ሕይወት መስዋትነት የደረሰ ተጋድሎ ፈጽሟል፣ ደማቅ ታሪካዊ አሻራውንም አሳርፎበታል።
ግድቡን 24 ሰዓት እየጠበቀ፣ ለግድቡ የሚያስፈልገውን የግንባታ መሣሪያዎች በማጀብ እያጓጓዘ፣ የአየር ክልሉን በውጭ ጠላት እንዳይደፈር በንቃት እየጠበቀ በጀግንነት ዘልቋል።
አሁን ላይ የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ተጠናቅቆ ለምረቃ በመድረሱ የመከላከያ ሠራዊት አባላት ደስታቸውን ገልጸዋል።
በብር ሸለቆ የመሠረታዊ ውትድርና ማሠልጠኛ ትምህርት ቤት ላይ አሚኮ ያገኛቸው የሀገር መከላከያ ሠራዊት አባል ሌተናል ኮሎኔል አብርሃም አንጄሎ የመከላከያ ሠራዊት ለታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ ታላቅ መስዋትነት ሲከፍል መቆየቱን ተናግረዋል።
የሕዳሴ ግድብ እና የኢትዮጵያ የሀገር መከላከያ ሠራዊት የአንድ ሳንቲም ሁለት ገጽታዎች ናቸው ነው ያሉት።
የኢትዮጵያ የሀገር መከላከያ ሠራዊት ግድቡን ከመጠበቅ አልፎ ሠራዊቱ የአካል፣ የገንዘብ እና የሕይወት መሥዋትነት ከፍሎ ለዚህ ያበቃው በመኾኑ ትልቅ ኩራት ይሰማናል ብለዋል።
የሕዳሴ ግድብ የተገነባው በተለያዩ መንገዶች ተጽዕኖ ከሚፈጥሩ ከዓለም ሀገራት ጋር በተለያዩ መንገዶች በተደረገ ትግል መኾኑንም አብራርተዋል።
በርካታ የውስጥ እና የውጭ ታሪካዊ ጠላቶች የታላቁ የኢትዮጵያ የሕዳሴ ግድብን ለማስተጓጎል ጥረቶች ማድረጋቸውን ጠቁመዋል።
የኢትዮጵያ የሀገር መከላከያ ሠራዊት መስዋዕትነት እየከፈለ ለዚህ አብቅቶታል ለዚህም ኩራት ይሰማናል ብለዋል።
“የታላቁ የኢትዮጵያ የሕዳሴ ግድብን ገንብቶ ማጠናቀቅ መቻሉ አባቶች ሠርተው ያለፉትን የዓድዋ ድል ታሪክ መድገም ነው በዚህም ምክንያት የታላቁ የኢትዮጵያ የሕዳሴ ግድብ መጠናቀቅ ዳግም የዓድዋ ድል እንደኾነ እቆጥረዋለሁ” ብለዋል።
ሌላኛው የኢትዮጵያ የሀገር መከላከያ ሠራዊት አባል ሻለቃ በኃይሉ ተፈራ የታላቁ የኢትዮጵያ የሕዳሴ ግድብ ብዙ ውጣ ውረዶችን አልፎ ለምረቃ በመድረሱ እንዳስደሰታቸው ነግረውናል።
በግድቡ ግንባታ የሀገር መከላከያ ሠራዊቱ ከገንዘብ አስተዋጽኦ በተጨማሪ እስከ ሕይወት መስዋትነት በመክፈል፣ ሌት ብርዱ ቀን ፀሐዩ እየተፈራረቀበት ለስኬት እንዲበቃ ትልቅ አስተዋጽኦ ማበርከቱን አብራርተዋል።
ግድቡ የኢትዮጵያን አንድነት እና ኅብረ ብሔራዊነት በተግባር የገለጠ ነው ብለዋል። ለመላው ኢትዮጵያውያን የብርሃን ምንጭ ስለመኾኑም ነው የተናገሩት።
ልማት ሲታሰብ ሰላም በቀዳሚነት ይመጣል፣ ሰላም ሲታሰብ ደግሞ የጸጥታ ኃይል ይነሳል፤ ለዚህ ደግሞ የሀገር መከላከያ ሠራዊት ከፍ ያለውን ድርሻ ይወስዳል ነው ያሉት።
የሕዝብ አብራክ ክፋይ የኾነው የኢትዮጵያ የሀገር መከላከያ ሠራዊት በሕዝብ ገንዘብ የተገነባውን የታላቁ የኢትዮጵያ የሕዳሴ ግድብ የመጠበቅ ግዴታ አለበት ብለዋል።
የኢትዮጵያ የሀገር መከላከያ ሠራዊት ግድቡ ከተጀመረ አንስቶ የሚጓጓዙ ቁሳቁሶችን እያጀበ ግድቡን በወትሮ ዝግጁነቱ እየጠበቀ ለዚህ አድርሶታል ነው ያሉት።
የታላቁ የኢትዮጵያ የሕዳሴ ግድብ እናቶች ከጭስ የሚገላገሉበት፣ በርካታ ፋብሪካዎች የሚገነቡበት፣ ለኢትዮጵያ ሁለንተናዊ ልማት የሚመጣበት እንደኾነም ነው አስተያየታቸውን የሰጡት።
ሌላኛው የኢትዮጵያ የሀገር መከላከያ ሠራዊት አባል ሻለቃ አምባቸው ዳምጤ ግድቡ ለኢትዮጵያውያን አዲስ ምዕራፍ የከፈተ እና ሌላ ተስፋ ይዞ የመጣ ክስተት ነው ይላሉ። ግድቡ ልዩ የኾነ የትውልድ ስጦታ ስለመኾኑም ነው የሚገልጹት።
መሥዋትነት ለሀገር እና ለሕዝብ ያለ ነው፤ ግድቡም አንዱ እየተሰዋ በቅብብሎሽ ሌላው እያስቀጠለው ለዚህ የበቃ ነው ይላሉ።
ግድቡ በስኬት መጠናቀቁ ከዚህም በላይ የመሥራት አቅም እንዳለ ያሳየ እንደኾነም ጠቁመዋል። በማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች ግድቡ ዋስትና ስለመኾኑም ነው የገለጹት።
የማይንበረከክ ትውልድ እንዲፈጠር የሕዳሴ ግድብ ተምሳሌት ስለመኾኑም ነው የኢትዮጵያ የሀገር መከላከያ ሠራዊት አባላት የተናገሩት።
ትውልድ ተሻጋሪ ሀሳብ መያዝ እና መግባባት ከተቻለ በብዙ ችግሮች ውስጥ ማለፍ እንደሚቻል ያሳየ ፕሮጀክት ስለመኾኑም የኢትዮጵያ የሀገር መከላከያ ሠራዊት አባላት አመላክተዋል።
ዘጋቢ: አሰፋ ልጥገበው
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን
Previous articleየትምህርት ስብራትን ለመጠገን በተከናወኑ ተግባራት አበረታች ውጤት መመዝገቡን ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለጹ።
Next articleርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ “የጎርጎራ ቃልኪዳን” ሰነድን ፈርመው ለከፍተኛ መሪዎች አስረከቡ።