ከባሕር ዳር አነስተኛ የንጹሕ መጠጥ ውኃ 38 በመቶው ይባክንባታል፡፡

131

ባሕር ዳር፡ ሰኔ 2/2012 ዓ.ም (አብመድ) ከ1950ዎቹ ጀምሮ የንጹሕ መጠጥ ውኃ ተጠቃሚ የሆነችው የባሕር ዳር ከተማ አስተዳደር የሕዝብ ቁጥሯ እየጨመረ እና ለኢንዱስትሪዎች የሚውል የውኃ ፍጆታም መጨመሩን ተከትሎ ለንጹሕ መጠጥ ውኃ እጥረት ተጋላጭ ሆናለች፡፡

60 ሺህ ሜትር ኩብ ውኃ በቀን ማግኘት ሲገባት 37 ሺህ ሜትር ኩብ ብቻ ነው የምታገኘው፤ ከእዚህም 38 በመቶ የሚባክን መሆኑ ደግሞ ከኢንዱስትሪዎች አልፎ ነዋሪዎችን አማርሯል፡፡ ከእንቅርት ላይ ጀሮ ደግፍ የሆነ የአሠራር እና አፈጻጸም ችግር መኖሩንም የክልሉ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች በመስክ ጉብኝት አረጋግጠዋል፡፡

በባሕር ዳር ከተማ አስተዳደር ዳግማዊ ምኒሊክ ክፍለ ከተማ ነዋሪዋ ወይዘሮ ጥሩየ ሲሳይ በውኃ እጥረት ምክንያት ለቀናት በወረፋ ለመቅዳት መገዳዳቸውን ተናግረዋል፡፡ የውኃ አለቃቅ ሥርዓቱም መቼ እንደሚመጣ ስለማያሳውቅ ሳይቀዱ የሚያልፋቸው ቀን እንዳለም ተናግረዋል፡፡ ወይዘሮ ጥሩየ የባሕር ዳር ውኃ እጥረት እንደሚያስገርማቸው ከመናገር ባለፈ ምክንያቱን እንደማያውቁት ነው የተናገሩት፡፡ የውኃ ችግሩ በባሕር ዳር የተለያዩ ክፍለ ከተሞችም ተመሳሳይ ችግር ያለበት ነው፡፡

አብመድ ያነጋገራቸው ነዋሪዎች ‘‘የዓባይን ልጅ ውኃ ጠማው …’’ ከማለት ባለፈ የንጹሕ መጠጥ ውኃ እጥረቱ ምክንያት ምን እንደሆነ እንደማያውቁ ተናግረዋል፡፡ ነዋሪዎች በየዓመቱ ከጥር በኋላ ለከፍተኛ የውኃ እጥረት እንደሚዳረጉ አብመድ ሲዘግብ ኖሯል፡፡ የባሕር ዳር የውኃ ጥም ምክንያት የአሠራር አፈጻጸም ችግር እና የረጅም ጊዜ ፍላጎትን ለመፍታት የሚያስችል በዕቅድ የታገዘ አመራር ያለመስጠት እንደሆነ አብመድ ታዝቧል፡፡

‘‘የከተማዋ የንጹሕ መጠጥ ውኃ እጥረት የውኃ ሀብት አለመኖር ብቻ ሳይሆን በ1994 ዓ.ም በተሠራው የውኃ አቅርቦት ላይ ብቻ እየጨመረ የመጣውን ኢንዱስትሪ እና ነዋሪ ለማስተናገድ መሞከሩ ነው’’ ያሉት የባሕር ዳር ከተማ አስተዳደር ውኃና ፍሳሽ ጽሕፈት ቤት የኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክተር በሪሁን ዓለሙ ናቸው፡፡ ከ15 ዓመታት በላይ ከከተማዋ ዕድገት ጋር የሚመጣጠን የውኃ አቅርቦት እንዲኖር አለመሠራቱ ችግሩ አሁን ላይ እንዲፈጠር ማድረጉንም ተናግረዋል፡፡ የባሕር ዳር ከተማ አስተዳደር የውኃ እጥረትን ለመፍታት ተጨማሪ የውኃ ምንጮች እንዲሠሩ ከመናገር ውጭ በጥናት የተደገፈ ፕሮጀክት ይዘው አለመቅረባቸውንም ገልጸዋል፡፡
ከተማዋ በቀን 60 ሺህ ሜትር ኩብ ውኃ እንደሚያስፈልጋት የተናገሩት ዳይሬክተሩ ከምታገኘው አነስተኛ ንጹሕ የመጠጥ ውኃም ‘‘38 በመቶ የሚሆነው በልዩ ልዩ ችግር ይባክናል’’ ብለዋል፡፡ የውኃ ብክነቱ ባለፉት ወራት እስከ 46 በመቶ ከፍ ብሎ እንደነበርም ተናግረዋል፡፡ የውኃ እጥረት ችግሩ ከሚያዝያ እስከ ሰኔ መጀመሪያዎች ላይ እንደሚበረታ አቶ በሪሁን አስታውቀው በእነዚህ ወቅቶች የጉድጓዶ እና የምንጮች አቅም በተፈጥሮ የሚቀንስበትና ደንበኞች ደግሞ ሙቀት በመሆኑ የውኃ አጠቃቀማቸው የሚጨምርበት መሆኑን አስረድተዋል፡፡

በባሕር ዳር ከተማ አስተዳደር የውኃ ብክነት የሚከሰተው ሕገ ወጦች ውኃው ከቆጣሪው ሳይደርስ ቱቦውን ቆርጠው ወዳዘጋጁት ታንከር በመውሰድ፣ ውኃው ከምንጮች እና ከጉድጎዶች ሲመጣ ከታንከሩ ሳይደርስ በውስጥ ለውስጥ ጠልፎ በመውሰድ፣ ቆጣሪ አንባቢዎች በአግባቡ ሳይቆጥሩ በመቅረታቸው የተከሰተ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ችግሩን ለመፍታት መስመሮችን መቆጣጠር የችል ቴክኖሎጂ እንደሚያስፈልጋቸውም ተናግረዋል፡፡ የከተማ አስተዳደሩን ይህንን ለማሟላት የበጀት አቅም እጥረት ያለው መሆኑንም ገልጸዋል፡፡

ችግሩን ለመቀነስ ግን ምንጮች የሚያመነጩት ውኃ በሕጋዊ መንገድ ለደንበኞች እንዲደርስ ዳግማዊ ምኒሊክና ክፍለ ከተማ እና ዘንዘልማ አካባቢ የጥበቃ ሠራተኞችን መቅጠራቸውን ተናግረዋል፡፡ ከፀጥታ ኃይሎች ጋር አብረው በመሥራታቸውም እስከ 5 የሚደርሱ ሕገ ወጦችን መቆጣጠር መቻላቸውንም ገልጸዋል፡፡ የውኃ ጠለፋው ሕገ ወጥ አሠራር ውስብስብ በመሆኑ ሁሉንም ሕገ ወጥ ሥራዎች ለመቆጣጠር ከባድ መሆኑንም አስታውቀዋል፡፡

የባሕር ዳርን የንጹሕ መጠጥ ውኃ እጥረት ለመፍታት በ2013 ዓ.ም እንደሚደርሱ በዕቅድ የተያዙ ሁለት ፕሮጀክቶች ሥራ ላይ መሆናቸውን የገለጹት የኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክተሩ የከተማዋን የውኃ እጥረት በዘላቂነት ለመፍታት ያረጁ ቧንቧዎችንና ነባር መሥመሮችን ጥናት በማድረግ ለመቀየር እየሠሩ መሆናቸውንም ተናግረዋል፡፡

ከሰሞኑ ፕሮጀክቶችን ተዘዋውረው የጎበኙት የአማራ ክልል ርእሰ መሥተዳድር ተመሥገን ጥሩነህ የባሕር ዳር ከተማን ጊዜያዊ የውኃ እጥረት ለመፍታት ሕገ ወጥ የንጹሕ መጠጥ ውኃ ብልሹ አሠራሮችን መቅረፍ እንደሚገባ ማሳሰባቸው የሚታወስ ነው፡፡ የሥራ ኃላፊዎች ከኅብረተሰቡ ጋር በመሆን ሕግ እና ሥርዓት ለማስከበር ሊሠሩ እንደሚገባ ያሳሰቡት ርእሰ መሥተዳደሩ ይህንን ማድረግ ባልቻሉት ኃላፊዎች ላይ መንግሥት ርምጃ እንደሚወስድ አስታውቀዋል፡፡

በባሕር ዳር ከተማ አስተዳደር የሚፈጸሙ የውኃ ብክነቶችን ለማስቀረት ማኅበረሰቡ በነጻ የስልክ መስመር 6814 መረጃዎችን እንዲያደርስም ከተማ አስተዳደሩ ጠይቋል፡፡

ዘጋቢ፡- ግርማ ተጫነ

ተጨማሪ መረጃዎችን
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m
ዩቱዩብ https://bit.ly/38mpvDC ያገኛሉ፡፡

Previous articleቺርቤዋ-ጉንቤት 30 ጌርክ 2012 ም. አ
Next articleበአማራ ክልል ባለፉት 24 ሰዓታት በ10 ሰዎች ላይ የኮሮናቫይረስ ተገኘባቸው፤ በ24 ሰዓታት ውስጥ ያገገምም ሆነ ሕይወቱ ያለፈ ሰውም የለም፡፡