
የክልሉን ሰላም ዘላቂ ለማድረግ የጸጥታ አካላትን አቅም በሥልጠና ለማሳደግ እየተሠራ ነው።
ደብረ ማርቆስ: ነሐሴ 25/2017 ዓ.ም (አሚኮ) “ባለሕልም የክልል የጸጥታ አመራር ለሁለንተናዊ እምርታ” በሚል መሪ መልዕክት በደብረ ማርቆስ ከተማ ለፀጥታ አካላት የአቅም ማጎልበቻ ሥልጠና መሥጠት ተጀምሯል።
በክልሉ የተፈጠረውን የጸጥታ ችግር ወደ ዘላቂ ሰላም ለመቀየር የጸጥታ አካላት መሪዎችን አቅም የሚያሳድግ ሥልጠና ነው በደብረ ማርቆስ ከተማ እየተሠጠ የሚገኘው።
በክልሉ የተፈጠረው የጸጥታ ችግር የሰው ሕይዎትን ጨምሮ የንብረት ውድመት ከማስከተሉም በተጨማሪ ማኅበራዊ እንቅስቃሴውን ገድቦት ቆይቷል፡፡
ችግሩንም ቀርፎ ዘላቂ ሰላም ለማረጋገጥ ለጸጥታ አማራሩ የአጭር እና የረዥም ጊዜ ሥልጠና ሲሰጥ ቆይቷል፡፡
የደብረ ማርቆስ ከተማ አሥተዳደር ሰላም እና ጸጥታ መምሪያ ኀላፊ እና ተወካይ ከንቲባ ይሄነው አበባው የጸጥታ መሪዎችን አቅም የሚያጎለብት እና ክፍተትን የሚሞላ ሥልጠና እየተሰጠ ነው ብለዋል።
ሥልጠናው ተቀራራቢ የጸጥታ ሥራ አፈጻጸም እንዲኖር ታሳቢ ያደረገ መኾኑንም ገልጸዋል፡፡
ተልዕኮ ላይ ግልጽ እና ቁርጠኛ የኾነ የጸጥታ ኀይል መፍጠር አስፈላጊ በመኾኑ ይህን ታሳቢ ያደረገ የማብቃት ሥራ እየተሠራ ስለመኾኑም አስገንዝበዋል።
የአመለካከት እና የአስተሳሰብ ዝንፈቶችንም ለማስተካከል የሚረዳ ሥልጠና መኾኑንም ገልጸዋል፡፡
የአማራ ክልል ሚሊሻ ጽሕፈት ቤት ምክትል ኀላፊ ገደቤ ኃይሉ የክልሉ የጸጥታ መሻሻል የመጣው የሀገር መከላከያ ሠራዊትን ጨምሮ በየደረጃው ያለው የጸጥታ መዋቅር ቅንጅታዊ ሥራ በመሥራቱ እንደኾነም ነው ያብራሩት።
ሠልጣኝ የጸጥታ መሪዎችም እንደ ክልል ከዚህ በፊት የታዩትን የጸጥታ ችግሮች በመለየት ጠንካራ እና ቁርጠኛ አመራር እንዲሰጡ ለማስቻል ታሳቢ ያደረገ ሥልጠና እየተሠጣቸው ስለመኾኑም ጠቁመዋል።
ግዳጅን መፈፀም የሚችል ሠራዊት መገንባትም የሥልጠናው አካል መኾኑንም ተናግረዋል፡፡
ለዚህም መሪዎች ሕዝብ የማገልገል ኀላፊነታቸውን መወጣት ይኖርባቸዋል ብለዋል፡፡ ዋጋ የከፈሉ የጸጥታ አካላትንም አመሥግነዋል፡፡
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን