“የሀገር ውስጥ ምርትን መግዛት የኢኮኖሚ ዕድገትን የማሳለጥ ጉዳይ ነው” ፕሬዝዳንት ታዬ አጽቀሥላሴ

12
አዲስ አበባ: ነሐሴ 24/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የኢፌዴሪ ፕሬዝዳንት ታዬ አጽቀሥላሴ በጥራት መንደር የተዘጋጀውን “የኢትዮጵያን ይግዙ” ሀገራዊ የንግድ ሳምንት ኤክስፖ አስጀምረዋል።
ከዛሬ ጀምሮ ለተከታታይ ስድስት ቀናት በሚቆየው ኤክስፖ የተዘጋጀውን ኤግዚቢሽን እና ባዛር ጎብኝተዋል።
በመርሐ ግብሩ ላይ መልእክት ያስተላለፉት የኢፌዴሪ
ፕሬዝዳንት ታዬ አጽቀሥላሴ የሀገር ውስጥ ምርት መግዛት እና መጠቀም ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታው የጎላ ነው ብለዋል። በምርት ላይ እሴት መጨመር ሀገራዊ ኢኮኖሚን የሚያደረጅ መኾኑንም ገልጸዋል።
የኢትዮጵያን ምርት ይግዙ ሲባል የሀገር ውስጥ ምርቶችን ጥራት ለማሳደግ የራስን አስተዋጽኦ አበርክቱ እንደማለት ነው ብለዋል።
የሀገር ውስጥ ምርትን መጠቀም የሥራ ዕድል በመፍጠር ለጤናማ ኢኮኖሚ ዕድገት መልካም ተስፋ መስጠት እንደኾነም ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ በዕድገት ምዕራፍ ላይ መኾኑን ያነሱት ፕሬዝዳንቱ ኢትዮጵያ በሀገራዊ ሪፎርሙ ታግዛ አበረታች ኢኮኖሚያዊ እና ማኅበራዊ ዕድገት ማስመዝገቧን ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ያስመዘገበችው ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ዓለም አቀፍ ተቋማት ጭምር ያረጋገጡት ለውጥ መኾኑን ገልጸዋል። በዚህም የወጭ ንግድን ጨምሯል፤ የዋጋ ግሽበት ቀንሷል ነው ያሉት።
የአፍሪካ አህጉራዊ ነፃ የንግድ ቀጣናን በፍጥነት ገቢራዊ በማድረግ እና የዓለም ንግድ ድርጅት አባልነት ድርድርን በፍጥነት በማጠናቀቅ የኢትዮጵያ ምርቶች ወደ ዓለም ገበያ የሚወዳደሩበትን መንገድ ማመቻቸት እንደሚገባም ተናግረዋል።
የሀገር ውስጥ ምርትን መጠቀም ሀገራዊ ሃብትን በማባዛት እና በማደራጀት የጎላ ትሩፋት ይኖረዋል ነው ያሉት።
አምራቾች የምርት ጥራት እና ፍጥነትን በማሳደግ የገበያ ድርሻቸውን እንዲያሳድጉ ጥሪ ያቀረቡት ፕሬዝዳንቱ መንግሥት አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግም አንስተዋል።
ሸማቾች የሀገር ውስጥ ምርት ሲገዙ የሀገራቸውን ኢኮኖሚ ከመደገፍ ባለፈ ለወገናቸው የሥራ ዕድል እየፈጠሩ መኾኑን እንዲረዱም አሳስበዋል።
ባለሃብቶች እና የፋይናንስ ተቋማት ከሀገር ውስጥ ባሻገር በአፍሪካ አህጉራዊ ነፃ የንግድ ቀጣና የሚሳተፋ አምራቾችን ለማፍራት በፋይናንስ ሊደግፉ ይገባል ብለዋል።
የንግድ ሥርዓቱን ማዘመን እና ኢኮኖሚን መገንባት ረጅም ጊዜ የሚፈጁ ቢኾኑም በኢትዮጵያ ግን ጅምሩ ሞገስ የሚሰጥ መኾኑንም ገልጸዋል።
መንግሥት ከመቸውም ጊዜ በላይ ምርት እንዲጨምር የሸማቹን ፍላጎት በተመጣጣኝ ዋጋ ለማርካት በትኩረት እንደሚሠራም አመላክተዋል።
በመርሐ ግብሩ በ2017 በጀት ዓመት የላቀ አፈጻጸም ላስመዘገቡ የንግዱ ማኅበረሰብ አባላት የዕውቅና እና የምሥጋና ሥነ ሥርዓት ተከናውኗል።
ዘጋቢ፦ ኢብራሂም ሙሃመድ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን
Previous articleብሔራዊ የጥራት መንደር ንግድ እና ኢንቨስትመንትን በማሻሻል እያገዘ ነው።
Next articleየክልሉን ሰላም ዘላቂ ለማድረግ የጸጥታ አካላትን አቅም በሥልጠና ለማሳደግ እየተሠራ ነው።