
ባሕር ዳር: ነሐሴ 24/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ለትምህርት ቅድሚያ የሰጡ ሀገራት በሥልጣኔ ላይ ሥልጣኔን አቀጣጥለዋል። የከበረ ታሪክ ሠርተዋል። ኢትዮጵያውያን ለትምህርት ታላቅ ትርጉም ይሰጣሉ በሀገር በቀል ዕውቀት ሲራቀቁ ኖረዋል። ምስጢር አሜስጥረዋል። በዕውቀት የነገውን ተንብየዋል። ይህን በማድረጋቸውም በዓለም ታሪክ ውስጥ በራሳቸው ዕውቀት ታውቀዋል።
እጓለ ገብረ ዮሐንስ የከፍተኛ ትምህርት ዘይቤ በተሰኘው መጽሐፋቸው የኢትዮጵያ ሕዝብ ከታሪካዊ ዕድሉ ለመድረስ ከዛሬው የሚበልጠውን የነገውን ትልቅነት በእጁ ለማድረግ በተምኔት እየተመራ ወደፊት ይጓዛል። ከዚህ ዓላማው ከሚያደርሱት መሣሪያዎች አንደኛው ትምህርት ነው፤ ሁለተኛው ትምህርት ነው፤ ሦሥተኛውም ትምህርት ነው ብለው ጽፈዋል። ትምህርት ቀላል ነገር አይደለም። ስለትምህርት ያለን አስተያየት ትክክለኛ ከኾነ ማናቸውም የሕይዎት ችግር ሊፈታ ይችላል። ሰው ከሙሉ የሰውነት ደረጃ የሚደርሰው በትምህርት ነው ይላሉ። ኢትዮጵያ እና ኢትዮጵያውያን ለትምህርት ትኩረት ሰጥተው ዘመናትን ተሻግረዋል። ነገር ግን ትምህርታቸው በተለያየ መልኩ ሲፈተን ኖሯል። ዛሬም እየተፈተነ ነው።
ደራሲ፣ ባለ ቅኔ እና ጸሐፈ ተውኔት ጋሽ አያልነህ ሙላቱ ትምህርት የአንድ ሀገር የዕድገት ብቻ ሳይኾን የሕልውና መጠበቂያ ነው ይላሉ። ሀገር የምትታወቀው፣ በዓለም ላይ ቦታ የሚኖራት፣ የምትወዳደረው በትምህርት እና በሥልጣኔ ነው ብለዋል። የአንዲት ሀገር ማንነት፣ ታሪክ፣ ባሕል፣ እሴት እና ወግ የሚገለጸው እና የሚነገረው በትምህርት አማካኝነት ነው። ትምህርት ለአንድ ሀገር ደምና ስጋ ነው፤ የሕላዌነቷ መገለጫም ነው ይላሉ። ያልተማረን ሕዝብ ማንም እንደፈለገ ያደርገዋል፤ በፈለገው መንገድ ይገዛዋል፤ በፈለገው አቅጣጫ ይወስደዋል የሚሉት ጋሽ አያልነህ ትምህርት ሲኖር ግን የሕዝብ ንቃተ ሕሊና ያድጋል፤ ለሥራ ይነሳሳል ነው የሚሉት።
ትምህርት መደበኛ እና ኢ-መደበኛም ሊኾን ይችላል፤ ነገር ግን የትኛውም ይሁን ትምህርት አስፈላጊ ነው፤ ከመደበኛም ኾነ ኢ መደበኛ የሚገኘው ዕውቀት የአንድ ሀገር መሠረት ነው ይላሉ። ኢትዮጵያ ጸንታ ያለችው መደበኛ የሚባለውን ትምህርት ባልተማረው ነው፤ ይህ ለኢትዮጵያ ጽናት መሠረት ነው፤ ስለዚህ ትምህርት ከየትም ይሁን አስፈላጊ ነው ብለዋል። በዚህ ዘመን በሚሊዮን የሚቆጠሩ ልጆችን ከትምህርት ገበታ ማራቅ አደጋው የከፋ ነው፤ ከሁሉም የሚከፋው እና የሚያሰጋው ግን ኢትዮጵያውያን ለዘመናት ይዘውት የኖሩት እሴት የጠፋ እንደኾነ ነው ይላሉ። ግጭት በተደጋገመ ቁጥር እሴት ይሟሟል፤ ይህ ደግሞ ያሳስበኛል ነው የሚሉት። ትምህርት ማግኘት የሚገባው ትውልድ ከትምህርት ገበታ ውጭ ኾኖ ሳይ ያሳዝነኛል፤ ይህ ትክክል አይደለም፤ ይህ ጉዳይ ሁሉንም ሊያሳስብ ይገባል፤ ፈጣን መፍትሄም ይሻል ነው የሚሉት።
ተማሪዎች ከትምህርት ገበታ በራቁ ቁጥር ሥራ አጥነት ይስፋፋል፤ ተጨማሪ ችግሮችም ይበዛሉ ይላሉ። የእኛ ሀገር የትምህርት ሥርዓት ኢትዮጵያ እና ኢትዮጵያውያንን መሠረት አድርጎ የተገነባ አይደለም የሚሉት ጋሽ አያልነህ ይህም ኢትዮጵያዊነትን ለመገንባት አቅም አንሶታል ብለዋል። የእኛ ዘመናዊ ትምህርት ከውጭ የተቀበልነው፣ ከእኛ ባሕል፣ እሴት እና ታሪክ ጋር የማይሄድ ስለኾነ የሠለጠነ ፖለቲካ እንድንገነባ አላደረገንም፤ ኢትዮጵያንም መገንባት አልቻለም ይላሉ። እኛ ዘመናዊ ትምህርት የምንለው የእኛን ከማሳወቅ ይልቅ የፈረንጆችን እንድናውቅ ነው የሚያደርግ፤ የእነርሱን ተምረን የእኛን ማወቅ አቃተን፤ የእኛን ስላላወቅን የራሳችን ችግር ለመፍታት ተቸገርን ነው የሚሉት።
ኢትዮጵያውያን ለዘመናት በጠላት ሳይገዙ ኖረዋል፤ ጠላቶች በተደጋጋሚ በጦርነት ሞክረዋል፤ በተደጋጋሚም ተሸንፈዋል፤ በአስኳላ ግን ወደ ሀገራችን ገቡ፤ ይህም ትምህርት እርስ በእርስ እንዳንስማማ አድርጎናል ይላሉ። ችግሮቻችን መፍታት ከፈለግን ሀገር በቀል ዕውቀትን እንገንባ፤ ሀገር በቀል ዕውቀት ስንገነባ ሀገር ሰላም ትኾናለች፤ ችግሮቻችንም በወግ ባሕላችን መሠረት መፍታት እንችላለን ነው የሚሉት። መነጋገር ያስፈልጋል፤ ስንነጋገር እንግባባለን የሚሉት ጋሽ አያልነህ እርቀ ሰላምን ከኬኔዲ ቤተ መጻሕፍት ሳይኾን አበው ካቆዩን ዛፍ ሥር እንፈልግ፤ ከታላላቅ ዛፎች ሥር የእኛ አስታራቂ ሽማግሌዎች አሉ፤ የእኛ መታረቂያ መንገድ ያ ነው፤ ከውጭ የመጣው እና የማናውቀው አያስታርቀንም ይላሉ።
ኢትዮጵያ እና ኢትዮጵያውያን ለዘመናት የቆዩ የችግር መፍቻ መንገዶች፣ ደም የሚያደርቁ የሽምግልና ሥርዓቶች አሉን፤ እነርሱን ተጠቅመን ሰላም እናምጣ፤ ያን ጊዜ ተማሪዎች ይማራሉ፤ ገበሬዎች ያርሳሉ፤ ነጋዴዎችም ይነግዳሉ ነው የሚሉት። የኢትዮጵያን እሴት እና ወግ ያልጣሉት የኢትዮጵያ ገበሬዎች ኢትዮጵያን ይዘውልን ቆመዋል ነው የሚሉት። በኢትዮጵያ ሰማይ ሥር ከ85 በመቶ በላይ በተፈጥሮ የተማረ፣ በሀገር ባሕል ሊቅ የኾነ ገበሬ ባይኖር የኢትዮጵያ አደጋ ይከፋ ነበር፤ በባሕል ሊቅ የኾነው ገበሬ ኢትዮጵያዊነትን ጠብቆ ይዟል ይላሉ። መደማመጥ ያስፈልገናል፤ ካልተደማመጥን ሀገራችን ከእጃችን ታመልጣለች፤ መደማመጥ ያልቻሉ ሕዝቦች ሀገራቸውን ከእጃቸው ላይ ጥለው ለማንሳት ተቸግረዋል፤ እኛ እንኳን አልደማመጥ ብለን እንዲያውም የሚዞሩን ጠላቶች አሉን ይላሉ።
ሰላምን በማስፈን ተማሪዎች ወደ ትምህርት ቤት እንዲመለሱ ማድረግ የሁሉም ጉዳይ መኾን እንደሚገባውም ገልጸዋል። ዘላቂ መፍትሔ ለማምጣት ደግሞ ሥርዓተ ትምህርቱን በሀገር በቀል ዕውቀት ላይ በመገንባት የቀጣዩን ትውልድ መቅረጽ ይገባል ነው ያሉት። የኢትዮጵያ ሀገር በቀል ዕውቀት የዘመናዊ ትምህርት መሠረት ካልኾነ ተመልሰን ችግር ውስጥ መግባታችን አይቀርም ነው የሚሉት። እኛ የአጼ ቴዎድሮስ መንፈስ ያስፈልገናል ያሉት ጋሽ አያልነህ አጼ ቴዎድሮስ ከዘመናት በፊት በኢትዮጵያ ሀገር በቀል ዕውቀት እንዲስፋፋ ጥረት አድርገው ነበር፤ ሁልጊዜም ከሰው እየተዋሱ መኖር ለኢትዮጵያ እንደማይጠቅማት ተረድተው ነበር፤ እኛም የእሳቸው መንፈስ እና ራዕይ ያስፈልገናል ነው ያሉት።
አጼ ቴዎድሮስ ክብርን ብቻ ሳይኾን ራዕይን ጭምር ነው ያወረሱን፤ የውጭ ነገሥታት መድፍ እንስጥህ ብለዋቸው ነበር፤ እርሳቸው ግን እኔ የሀገሬ ጠቢባን እያዩት የሚሠራ እና በሀገሬ የሚሠራ መድፍ ነው የምፈልገው ብለው እምቢ አሉ፤ ሀገር በቀል ዕውቀት ማለት ይህ ነው ይላሉ።
የሥልጣኔ መሠረት የሀገር በቀል ዕውቀት ነው፤ ሀገር በቀል ዕውቀትን መሠረት አድርገን ሰላማችን እናጽና፤ ሥልጣኔያችንም እንገንባ ነው ያሉት። ልጆች እንዲማሩ ሰላምን ማስፈን ግድ ይላል፤ ሰላምን የሚያሰፍኑት ደግሞ ሁሉም ሲተባበሩ ነው ብለዋል።
ዘጋቢ፦ታርቆ ክንዴ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን