
ጎንደር: ነሐሴ 24/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የመንግሥትን የሰላም ጥሪ የተቀበሉ ታጣቂዎች በጎንደር ከተማ የተሐድሶ ሥልጠና ጀምረዋል።
በማስጀመሪያ በመርሐ ግብሩ ላይ የአማራ ክልል ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ይርጋ ሲሳይ፣ የአማራ ክልል ምክር ቤት ምክትል አፈ ጉባኤ አማረ ሰጤ፣ የብሔራዊ ተሐድሶ ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር ጀኔራል ደርቤ መኩሪያው፣ የአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ አዛዥ ዘላለም መንግሥቴ (ዶ.ር)፣ የአማራ ክልል ሰላም እና ጸጥታ ቢሮ ምክትል ኀላፊ በሪሁን መንግሥቱ እና ሌሎችም የክልሉ ከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎች፣ የዞን እና የከተማ አሥተዳደር የሥራ ኀላፊዎች፣ የሃይማኖት አባቶች እና የሀገር ሽማግሌዎች ተገኝተዋል።
የብሔራዊ ተሐድሶ ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር ጀኔራል ደርቤ መኩሪያው በመርሐ ግብሩ እንደተናገሩት የብሔራዊ ተሐድሶ ኮሚሽን በ2015 ዓ.ም የተመሠረተ ሲኾን ዋና ዓላማው የታጠቁ ቡድኖች እና ግለሰቦች ወደ ሰላም እንዲመጡ ማድረግ እና ግለሰቦቹ በዘላቂነት እንዲቋቋሙ መሥራት ነው ብለዋል።
ጀኔራሉ በአማራ ክልል በሦስት ማዕከላት ከ6 ሺህ በላይ የሰላም ጥሪውን የተቀበሉ ታጣቂዎች የተሐድሶ ሥልጠና እንደሚሰጣቸውም ገልጸዋል። ታጥቀው የወጡ አካላትን ወደ ሰላማዊ መንገድ ለማምጣት በተሠራው ሥራ “ከ72 ሺህ በላይ ለሚኾኑ ታጣቂዎች የተሐድሶ ሥልጠና መሰጠቱንም” ተናግረዋል። ለዚህም ከ7 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር በላይ ወጭ መኾኑን ጠቁመዋል።
የታጠቁ አካላት ወደ ሰላም እንመጡ ከሃይማኖት አባቶች እና ከሀገር ሽማግሌዎች ጋር በመኾን ለሰላም መስፈን መሠራቱን ያነሱት ጀኔራል ደርቤ ታጣቂዎቹ የሰላምን አማራጭ መርጠው የመንግሥትን የሰላም ጥሪ በመቀበላቸው ሊመሰገኑ ይገባል ብለዋል።
የተሐድሶ ሠልጣኞች ከሥልጠናው ባሻገርም እንዲቋቋሙ የማድረግ ተግባር ይሠራል ብለዋል። ሠልጣኞቹ ሀገራቸውን እና ሕዝባቸውን መካስ እንደሚገባቸውም አሳስበዋል። ችግሮች ቢኖሩም እንኳ በውይይት እና በሰላማዊ መንገድ መፍታት እና ሰላማዊ አማራጭን መምረጥ ይገባል ነው ያሉት።
መንግሥት ያቀረበውን የሰላም ጥሪ ተከትሎ የሰላምን አማራጭ ከተቀበሉ የማዕከሉ ሠልጣኞች መካከል አብዮት ዓለምነው እና ሻምበል ውበቴ ለሁለት ዓመታት ያክል ታጥቀው ጫካ መቆየታቸውን አስታውሰዋል። የመረጡት የስህተት መንገድ የአማራ ክልልን ሕዝብ የጎዳ እና የበርካቶችን ሕይዎት የነጠቀ በመኾኑ መጸጸታቸውን ተናግረዋል።
መንግሥት ያቀረበውን የሰላም ጥሪ ተቀብለው ሕዝብ እና መንግሥትን ለመካስ ቁርጠኛ መኾናቸውንም ገልጸዋል። ሌሎችም መንግሥት ያቀረበውን የሰላም ጥሪ እንዲጠቀሙ ማድረግ እንደሚገባም መልዕክት አስተላልፈዋል።
ዘጋቢ:- ቃልኪዳን ኃይሌ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!