መሃይምነትን ማንም መደገፍ የለበትም፤ የትምህርት ጉዳይ ለድርድር መቅረብም የለበትም።

12
ባሕር ዳር: ነሐሴ 24/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በበርካታ ችግሮች ውስጥ የቆየው የትምህርት ጉዳይ ዛሬም ስር ነቀል ለውጥን ይሻል። ይህን በማስተካከል ረገድ ድርሻው የአንድ አካል ብቻ ሳይኾን የሁሉም ነው።
የአማራ ክልል ሴቶች ማኅበራት ፌዴሬሽን ጽሕፈት ቤት ዋና ዳይሬክተር እነየ ገነቱ ፌዴሬሽኑ እስከ ቀበሌ ድረስ ባለው አደረጃጀት ለትምህርት ምዝገባው በትኩረት እየተንቀሳቀሰ እንደኾነ ከአሚኮ ጋር በነበራቸው ቆይታ ተናግረዋል። ከአጋር ተቋማት ጋር በተደረገው የትምህርት እንቅስቃሴም የተማሪዎች ምዝገባ ላይ ውጤት እየተመዘገበ እንደኾነም ገልጸዋል። ፌዴሬሽኑ በስሩ ሰባት አባል ማኅበራት ያሉት ሲኾን በተቀመጠው ግብ መሠረት ለምዝገባው ስኬት በትኩረት እንዲንቀሳቀሱ የማድረግ ሚናውን እየተወጣ እንደሚገኝም አንስተዋል። አንድም ሕጻን በዚህ ዓመት ከትምህርት መስተጓጎል የለበትም የሚል ሃሳብ በማንገብ በቁርጠኝነት ምዝገባ እያስኬዱ እንደሚገኙ ነው ዳይሬክተሯ የተናገሩት።
እስከ ነሐሴ 30/2017 ዓ.ም ድረስ የንቅናቄ እና የምዝገባ ተግባሩን የማገዝ እና ኀላፊነትን የመወጣት ተግባሩ ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።
በዚህ አካሄድም ከተቀመጠው ቀን ቀድመው የሚጨርሱ አካባቢዎች እንደሚኖሩ እያስተዋልን እንገኛለን ነው ያሉት ዳይሬክተሯ። ልጆችን ወደ ትምህርት ቤት ማስገባት ዋናው የሴቶች የፌዴሬሽን አቅጣጫ መኾኑንም ተናግረዋል። ፌዴሬሽኑ ከተማሪ ምዝገባው በሻገር ለትምህርት መሟላት የሚገባቸው ግብዓቶች እንዲሟሉም ጥረት እያደረገ ይገኛል ነው ያሉት። እናቶች ልጆቸቻቸውን ወደ ትምህር ቤት እንዲልኩ እና አቅማቸውን አሟጠው እንዲጠቀሙ ግንዛቤ ተሰጥቷል ብለዋል።
ያ መኾኑም አሁን በየአካባቢው ለመጣው የምዝገባ ውጤት አጋዥ እንደነበር ጠቁመዋል። እናቶች ከነበሩ ስጋቶች ወጥተው ትምህርትን በድፍረት እንዲደግፉ ተሠርቷል ነው ያሉት። ልጆች ዛሬ ካልተማሩ ከራሳቸው አልፎ ለቤተሰብም ኾነ ለሀገር ጉዳቱ ከፍተኛ መኾኑን ነው የገለጹት። ለቤተሠብ ትልቁን መሠረት የምትጥለው እናት ናት የሚሉት ወይዘሮ እነየ ልጆቿን እሷ በምትፈልገው መንገድ መምራት ትችላለችና ተሰሚ ናት ይላሉ። “በባሕላችንም ኾነ በወጋችን መሠረት እናት በልጇ ዘንድ ተሰሚ ናት” በዚህ ወቅት እናቶች ለትምህርት መከፈት ትልቅ ሚና ሊጫወቱ ይገባል ብለዋል። ለጉዳዩ እናቶች ትኩረት ካልሰጡ ግን ሙሉ ውጤት ለማምጣት እንደሚያስቸግርም ነው የገለጹት። እነሱ ሳይማሩ ለትምህርት የተሻለ ግንዛቤ ያላቸው ወላጆች ብዙ ናቸው ነው ያሉት።
የእነዚህን ወላጆች ሃሳብ መደገፍ እና መተግበር እንደሚገባም አስገንዝበዋል። በልጆች ጫማ ላይ ቆሞ የትምህርት መቋረጥ ሲታሰብ እጅግ ይከነክናል ብለዋል ዳይሬክተሯ። ልጆች እነሱ ባልፈቀዱት እና ባልሠሩት ነገር ሕይዎታቸው እንዲመሰቃቀል የማድረጉ ተግባር ሊወገዝ የሚገባው ነው ብለዋል። ትናንት ሳይማሩ ያስተማሩ ወላጆቻችን በነበሩባት ሀገር ዛሬ ፊደል በቆጠሩ ሰዎች የትምህርት ጉዳይ ጥያቄ ውስጥ መግባት የለበትም ነው ያሉት ወይዘሮ እነየ። ሀገር እዚህ የደረሰችው ያልተማሩ ገበሬዎች ባስተማሯቸው ልጆች አማካኝነት ነው ብለዋል። “መሃይምነትን ማንም መደገፍ የለበትም” ብለዋል። የትምህርት ጉዳይ ለድርድር መቅረብ የሌለበት እንደኾነም ነው የገለጹት።
ዘጋቢ፦ ሰለሞን አንዳርጌ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን
Previous articleየኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ደብረ ማርቆስ ዲስትሪክት በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ለሚገኙ ወገኖች የበዓል መዋያ ድጋፍ አደረገ።
Next articleየብር ሸለቆ ወታደራዊ ማሠልጠኛ ትምህርት ቤት ያሠለጠናቸውን መሠረታዊ ወታደሮች አስመረቀ።