
ደብረ ማርቆስ: ነሐሴ 24/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ደብረ ማርቆስ ዲስትሪክት ለ2018 ዓ.ም የዘመን መለወጫ የበዓል መዋያ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ለሚገኙ ወገኖች ድጋፍ አድርጓል።
ባንኩ 1 ነጥብ 3 ሚሊዮን ብር ወጭ በማድረግ በደብረ ማርቆስ ከተማ አሥተዳደር ለሚገኙ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ሕይዎታቸውን ለሚመሩ ወገኖች ነው የበዓል መዋያ ድጋፍ ያደረገው። ባንኩ ከዚህም በፊት በተለያየ ጊዜ ድጋፍ ሲያደርግ መቆየቱን የተናገሩት የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ደብረ ማርቆስ ዲስትሪክት ዳይሬክተር አፈወርቅ ሰንደቁ ናቸው። ድጋፍ የተደረገው ለ228 ወገኖች ሲኾን ለእያንዳንዳቸው 25 ኪሎ ግራም ዱቄት፣ አምስት ሊትር ዘይት እና 1 ሺህ 300 ብር ነው። ባንኩ ለማኅበረሰቡ የፋይናንስ ተደራሽነትን ለማረጋገጥ ከሚያከናውነው ተግባር በተጨማሪ ማኅበራዊ ኀላፊነቱንም እየተወጣ እንደሚገኝ ዳይሬክተሩ ገልጸዋል። ድጋፍ የተደረገላቸው ወገኖችም በተሰጣቸው ስጦታ በዓልን በደስታ ለመዋል እንደሚያስችላቸው ገልጸዋል። ስለተደረገላቸው ድጋፍም ምስጋና አቅርበዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!