ለሕዝብ ደኅንነት የሚጨነቅ ሁሉ ሰላማዊ አማራጭን ሊከተል ይገባል።

10
ባሕር ዳር: ነሐሴ 24/2017 ዓ.ም(አሚኮ) በኢትዮጵያ ውስጥ ባለፉት ዓመታት የተፈጠሩ አለመግባባቶች ሌላ ግጭቶችን እየወለዱ ሰላም ጠፍቶ ቆይቷል። የእርስ በርስ ግጭቱ እንደ ሀገር ሰብዓዊ እና ምጣኔ ሃብታዊ ውድመትን አስከትሏል።
በዚህም የአማራ ክልል አንዱ ገፈት ቀማሽ ኾኖ ቆይቷል። በተለይም ባለፉት ሁለት ዓመታት በክልሉ በተከሰተው ግጭት ሰብዓዊ እና ቁሳዊ ውድመት ደርሷል። የችግሩ ሰለባ ከኾኑ ዞኖች ውስጥ ደግሞ ሰሜን ሸዋ ዞን አንዱ ነው። የዞኑ ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ኤሊያስ አበበ ባለፉት ሁለት ዓመታት ባጋጠመው የጸጥታ ችግር የሰው ሕይዎት አልፏል፤ የንብረት ውድመትም ደርሷል፤ ማኅበረሰቡም ለምጣኔ ሃብታዊ እና ለማኅበራዊ ቀውስ ተጋልጦ ቆይቷል ብለዋል። በግጭቱ የደረሰውን ጉዳት ሕዝብ እንዲረዳው እና ማኅበረሰቡ ራሱ ለሰላም ዘብ እንዲቆም ሢሠራ ቆይቷል ነው ያሉት። በተሠራው ተግባርም በጫካ የነበሩ የታጠቁ ወገኖች በሰላም ወደ ማኅበረሰቡ እንዲቀላቀሉ ተደርጓል ብለዋል። ከሰሞኑም በርከት ያለ ቁጥር ያላቸው የታጠቁ ወገኖች የሰላም ጥሪውን ተቀብለው መግባታቸውን አንስተዋል።
የሰላም አማራጭ የተከተሉትን ወገኖች ሥልጠና በመስጠት ወደ ማኅበረሰቡ ተቀላቅለው መደበኛ ሕይዎት እንዲኖሩ እየተሠራ ይገኛል ነው ያሉት። አሁን ላይ አብዛኛው በዞኑ የሚገኙ ወረዳዎች ወደ ተሟላ ሰላም ተመልሰዋል ብለዋል ኀላፊው። አገልግሎት አቋርጠው የነበሩ የመንግሥት ተቋማትም በሙሉ አቅም ወደ ሥራ እንዲገቡ መደረጉን ነው የገለጹት። በቀጣይ በአንዳንድ አካባቢዎች የቀሩ የታጠቁ ቡድኖች የሰላም አማራጭን እንዲከተሉ እየተሠራ ይገኛል ብለዋል። የታጠቁ ወገኖች ሰላማዊ መንገድን እንዲከተሉም ጥሪ አቅርበዋል። የኦሮሞ ብሔረሰብ አሥተዳደር ዋና አሥተዳዳሪ አሕመድ አሊ ባለፉት ዓመታት የታጠቁ ቡድኖች ከብሔረሰብ አሥተዳደሩ ባለፈ በአጎራባች ዞኖች የሚገኙ የኅብረተሰብ ክፍሎችን ሰላም ሲያውኩ እንደቆዩ አስታውሰዋል።
ችግሩን ለመፍታት ከሰሜን ሸዋ እና ደቡብ ወሎ ዞኖች እና ከአፋር ክልል ጋር ጭምር በመቀናጀት በተሠራው ተግባር የማኅበረሰቡን ሰላም ሲያወኩ የነበሩ ቡድኖች ወደ ሰላም እንዲመለሱ ተደርጓል ብለዋል። ለዚህ ደግሞ የሀገር ሽማግሌዎች ብሎም የማኅበረሰቡ አስተዋጽኦ ከፍተኛ እንደነበር ነው የገለጹት። የሰላምን አማራጭ በማይከተሉት ላይ ደግሞ የጸጥታ መዋቅሩ ከማኅበረሰቡ ጋር በመቀናጀት የሕግ ማስከበር ተግባር መሠራቱንም ገልጸዋል። አሁንም የታጠቁ ቡድኖች በነፍጥ የሚመጣ ለውጥ አለመኖሩን ተረድተው የሰላም መንገድን እንዲከተሉ ጠይቀዋል።
ለሕዝብ ደኅንነት የሚጨነቅ ሁሉ ሰላማዊ አማራጮችን ሊከተል ይገባል ነው ያሉት።
ዘጋቢ: ዳግማዊ ተሠራ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
Previous articleዓባይ ባንክ እና ቪዛ ኢንተርናሽናል ለአምስት ዓመታት አብሮ ለመሥራት የሚያስችል ስምምነት ተፈራረሙ።
Next articleየኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ደብረ ማርቆስ ዲስትሪክት በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ለሚገኙ ወገኖች የበዓል መዋያ ድጋፍ አደረገ።