
ባሕር ዳር: ነሐሴ 23/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል የ25 ዓመታት አሻጋሪ እና የዘላቂ ልማት ዕቅድ አቅዶ ወደ ትግበራ ገብቷል። ዕቅዱም የትውልድ ቁጭትን ለትውልድ ልዕልና የማነጽ ትልም የያዘ ነው ተብሏል።
የአማራ ክልል ፕላን እና ልማት ቢሮ የሕዝብ ግንኙነት እና ኮሙዩኒኬሽን ኀላፊ ሞገስ አያሌው እቅዱ የረጅም፣ የመካከለኛ እና የአጭር ዘመን ዕቅዶችን ትስስር የሚያሳይ ነው ብለዋል። ዕቅዱ ከሌላው ጊዜ በተለየ መልኩ ለጥቅል ኢኮኖሚ ማዕቀፍ ግብ ስኬት ሚና ያላቸው የዘርፉ ልማት ዋና ዋና ግቦች ላይ ማተኮሩንም ገልጸዋል። በእቅድ ከተያዙ ግቦች ውስጥ አንዱ ደግሞ ትምህርት ነው ብለዋል።
በትኩረት ለመያዙ ምክንያቱ ትምህርት የዕውቀት ማሸጋገሪያ እና የፍትሐዊ ሃብት ክፍፍል ማረጋገጫ በመኾኑ ነው ብለዋል ኀላፊው። ትምህርት የኢኮኖሚ እና የሥልጣኔ ተስተካካይነት ማረጋገጫ መሳሪያ እና የርትዕ ማኅበረሰብ መቅረጫ ተቋም እንደኾነም ገልጸዋል፡፡ የትምህርት ጥራት ዋናው የሰብዓዊነት ግንባታ አምድ ቢኾንም ከብዙ አቅጣጫዎች ችግር ውስጥ ገብቷል ያሉት ኀላፊው ትምህርትን እንደ አዋጭ ኢንቨስትመንት በወጥነት ያለመቁጠር አመለካከት መኖሩን አንስተዋል። የመንግሥት የሠለጠነ የሰው ኃይል አቅርቦት እና የኢኮኖሚ መዋቅሩ የሰው ኃይል ፍላጎት አለመጣጣም የተማረ ሥራ አጥነት እንዲፈጠር ማድረጉንም ገልጸዋል። የትምህርት ሽፋን እና ፍትሐዊነት በሚፈለገው ደረጃ አለመድረስ እንዲሁም የትምህርት ጥራት ችግር መኖርም ሌላው የትምህርት ትልቅ እንቅፋት ኾኖ ቆይቷል ነው ያሉት።
የልዩ ፍላጎት ትምህርት በጣም ዝቅተኛ መኾን፣ ተግባር ተኮር የጎልማሶች ትምህርት እና ሥልጠና በቂ ትኩረት አለማግኘትም በችግር ከተጠቀሱ ጉዳዮች ውስጥ ናቸው ብለዋል። እነዚህን ችግሮች በመቅረፍ የተያዘውን ዕቅድ በውጤታማነት ለማሳካት ትምህርት ቤቶች በሂደት በተማሪዎች የሚወደዱ እና ለሁለንተናዊ ዕድገት ምቹ እንዲኾኑ የማድረግ ሥራ መሥራት ይጠበቃል ነው ያሉት። የትምህርት ተደራሽነት እና ሽፋንን ከጥራት እና ተጨባጭ ግብ ጋር በማመጣጠን ሚዛን የጠበቀ የትምህርት ሥርዓትን በማስፈን የሥርዓተ ትምህርት ፖሊሲን በአጽንኦት መተግበር፣ በትምህርት እና ሥልጠና ለአምራች ኢንዱስትሪ ልማት፣ ለግብርና ልማት፣ ለቱሪዝም ልማት፣ ለቴክኖሎጂ ሽግግር እና ዕድገት ብቁ የኾነ የተማረ የሰው ኀይል ማፍራት ይጠበቅብናል ብለዋል።
ሳይንሳዊ ዕውቀት እና ማኅበረሰባዊ ርትዕነትን (ግብረ ገብነት) ያዋሃደ የትምህርት ሥርዓትን በመዘርጋት ጥራት ያለው ትምህርት እና ሥልጠና ለሁሉም ዜጋ በፍትሐዊነት ተደራሽ ማድረግ እንደሚገባም ገልጸዋል። ዕቅዱ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ የኾኑ ብቁ ዜጎችን ማፍራት የትኩረት አቅጣጫው አድርጎ እንደሚሠራም ተናግረዋል። ዕቅዱን በውጤታማነት በመፈጸም የዓለም አቀፍ የዕውቀት እና ቴክኖሎጅ አቅጣጫን ግምት ውስጥ ያስገባ የተማረ የሰው ኃይልን ማፍራት ያስፈልጋል ነው ያሉት።
ዘጋቢ፦ ሰናይት በየነ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!