ሕገ ወጥ የነዳጅ ግብይትን በቅንጅታዊ አሠራር መቆጣጠር ይገባል።

14
ባሕር ዳር: ነሐሴ 23/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ንግድ እና ገበያ ልማት ቢሮ ከተለያዩ መንግሥታዊ እና መንግሥታዊ ካልኾኑ ተቋማት የሥራ ኀላፊዎች፣ የነዳጅ ባለ ማደያዎች እና የጸጥታ ኀላፊዎች ጋር በባሕር ዳር ከተማ ውይይት አድርጓል።
የውይይቱ ተሳታፊዎች በክልሉ እየተከናወኑ የሚገኙ የመንገድ፣ የመስኖ፣ የግብርና እና ሌሎችም የፕሮጀክት ሥራዎች በየጊዜው በሚገጥመው የነዳጅ እጥረት እየፈተኑ መኾናቸውን ተናግረዋል። በተለይ የተለያዩ የመሠረተ ልማት ሥራዎች ነዳጅ በወቅቱ ማግኘት ባለመቻላቸው መጠናቀቅ ከነበረባቸው ጊዜ በላይ ወስደዋል ነው ያሉት። ስለኾነም በመንግሥት እና በተገልጋዩ ኀብረተሰብ ዘንድ ዘርፈ ብዙ ችግር ተከስቷልም ብለዋል።
ወደ አማራ ክልል የሚላከውን የነዳጅ ድርሻ ከፌዴራሉ መንግሥት ጋር በመነጋገር ከክልሉ ሕዝብ የፍላጎት መጠን ጋር ማጣጣም እንደሚገባም ተሳታፊዎቹ ተናግረዋል።
ነዳጅ በማደያዎች እያለ እንኳ “የለም” እያሉ ምርቱን በመከዘን በጥቁር ገበያ የሚሸጡ እንዳሉም ተሳታፊዎቹ ጠቁመዋል። በመኾኑም በነዳጅ ግብይት እና ስርጭት ላይ ከፍተኛ ቁጥጥር እና ክትትል በማድረግ በአጥፊዎች ላይ አስተማሪ ርምጃ እንዲወሰድ ነው የጠየቁት። የነዳጅ ግብይቱን ዲጂታላይዝድ በማድረግም በሕገ ወጥ መንገድ ነዳጅ የሚሸጡትን ማደያዎች፣ ተገልጋዮች እና ደላላዎችን መቆጣጠር እንደሚቻልም አስገንዝበዋል። ሕግ አስከባሪዎችም ነዳጅ እንደ ሳሙና መንገድ ዳር በይፋ ሲሸጥ እያዩ እንዳላዩ ከማለፍ ለሕሊናቸው እና ለሕግ ተገዥ በመኾን ተከታትለው ለሕግ ማቅረብ አለባቸው ነው ያሉት።
ከአማራ ክልል ፖሊስ ጠቅላይ ዋና መምሪያ የተወከሉ የሥራ ኀላፊ ውይይቱ የችግሩን ምንጭ ያመላከተ እና የመፍትሔ ሃሳብ የጠቆሙ በመኾኑ ለጸጥታ ኀይሉ ጥሩ ግብዓት የተገኘበት ነው ሲሉ ተናግረዋል። ካሁን በፊት ሕገ ወጥ የነዳጅ ግብይት እና ስርጭት የተከሰተው የሚመለከታቸው አካላት ተቀናጅተው ባለመሥራታቸው ነው ያሉት የፖሊስ ተወካዩ ነዳጅ ተኮር ሁለንተናዊ እንቅስቃሴ እንዳይቆም በቀጣይም በግብረ ኀይል እየተገመገመ በዘላቂነት መመራት አለበት ብለዋል። የጸጥታ ኀይሉ ደግሞ ሕግ ለማስከበር ሁሌም በተጠንቀቅ ዝግጁ እንደኾነም ጠቁመዋል።
የአማራ ክልል ንግድና ገበያ ልማት ቢሮ ምክትል ኀላፊ ፈንታው ፈጠነ በ2017 በጀት ዓመት በክልሉ በየነዳጅ አይነቱ በልዩ ኹኔታ ታቅዶ መቅረቡን አስታውሰዋል።
ነዳጅ በፌዴራል መንግሥት ደረጃ በተፈቀደ የዲጂታል ሲስተም እንዲሸጥ ቢወሰንም የተዘረጋውን የአሠራር ሂደት ጠብቆ አለመሸጥ እንደነበር ምክትል ቢሮ ኀላፊው ተናግረዋል። ይሁንና ችግሩን ለማረም በየደረጃው እየተገመገመ ሥራዎች ተከናውነዋል ነው ያሉት። ነዳጅ እያለ የለም በሚሉት ማደያዎች ላይም አሥተዳደራዊ ርምጃ መወሰዱን ነው አቶ ፈንታው የተናገሩት። ሕግ እና አሠራር የማስከበሩ ሂደትም ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል። ነዳጅ ማደያ ባለበት በየትኛውም ከተማ ነዳጅ በችርቻሮ መሸጥ እንደለሌበት ሕግ መደንገጉንም ነው ኀላፊው የተናገሩት።
ማንኛውም ቀናዒ ዜጋ ነዳጅ በሕገ ወጥ መንገድ ሲሸጥ በመጠቆም መተባበር አለበት ነው ያሉት።
ለዚህ ተግባር ተብሎ የተቋቋመው ግብረ ኀይል ሕጉን መሠረት አድርገው ሥርዓት በማስከበር አጥፊዎችን ለሕግ ማቅረብ ይኖርባቸዋል ብለዋል።
ከፊታችን መስከረም 2018 ዓ.ም ጀምሮም ሁሉም የመንግሥት ተቋማት ፕሮጀክቶችን ጨምሮ ግብይት የሚፈጸመው በዲጂታል ሥርዓት ይኾናል ነው ያሉት። በ2017 በጀት ዓመት 267 ሚሊዮን ሊትር ናፍጣ፣ 64 ሚሊዮን ሊትር ቤንዚን እና 3 ነጥብ 7 ሚሊዮን ሊትር ነጭ ጋዝ ለአማራ ክልል መቅረቡን ምክትል ቢሮ ኀላፊው አስታውሰዋል።
ዘጋቢ፦ ሙሉጌታ ሙጨ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን
Previous articleየምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመሥገን ጥሩነህ መልእክት፦
Next articleብቁ ዜጎችን ማፍራት የ25 ዓመታቱ የአሻጋሪ እና የዘላቂ ልማት ዕቅዱ የትኩረት አቅጣጫ ነው።