
ባሕር ዳር፡ ነሐሴ 23/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ምክትል ጠቅላይ ሚኒስተር ተመሥገን ጥሩነህ በአማራ ክልል የመንግሥትን የሰላም ጥሪ የተቀበሉ ታጣቂዎችን አስመልክተው የሚከተለውን መልእክት አስተላልፈዋል።
የሰላምም ጀግና አለው!
ከጦርነት በላይ ሰላም ዋጋ ያስከፍላል። ትዕግሥት ያስጨርሳል፤ ትከሻ ያጎብጣል፤ እልክን ያስውጣል፤ ደካማ ያስመስላል። ለዚህ ነው የሰላም ጀግንነት ከጦርነት ጀግንነት የሚበልጠው። ሰላማዊ አማራጭን የተከተሉ፣ ሐሳባቸውን በጠረጴዛ ዙሪያ ለማቅረብ የፈቀዱ፣ የሠለጠነውን መንገድ ለመሞከር የቆረጡ ታጣቂዎች ሰሞኑን ወደ ተሐድሶ ማዕከላት እየገቡ ነው። ይህ የሰላም ጀግንነት በመሆኑ ከአድናቆት ጋር እናመሰግናቸዋለን። በዚህ ውሳኔያቸው ሀገር ታተርፋለች፣ እናት ትጽናናለች፣ መሬትም ታርፋለች። በዚህ ውሳኔያቸው አዲስ የሰላም ጀግንነት ታሪክ ይጽፋሉ።
ሌሎችም የእነርሱን አርአያ ተከትለው የሰላምን አማራጭ እንደሚመርጡ እናምናለን። የዘመናችን ትልቁ ጀግንነት የሰላም ጀግንነት ነውና።
የሰላም ጀግንነትን ዐውቀው ለወሰኑ፣ ላስተባበሩ፣ መርቀው ለተቀበሉ፣ ለሰላም እና ለሕግ የበላይነት ሁሌም የማይናወጥ አቋሙን ላሳየው ሕዝባችን የከበረ ምስጋና አቀርባለሁ።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!