
ባሕር ዳር: ነሐሴ 23/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በአማራ ክልል በተፈጠረው የጸጥታ ችግር በሚሊዮን የሚቆጠሩ ተማሪዎች ከትምህርት ገበታ ውጭ ኾነው ቆይተዋል። በሺዎች የሚቆጠሩ ትምህርት ቤቶች ደግሞ ጉዳት ደርሶባቸዋል።
ከትምህርት ገበታ ውጭ ኾነው የኖሩ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ተማሪዎችን በ2018 የትምህርት ዘመን ወደ ትምህርት ገበታ ለመመለስ እየተሠራም ነው። በባሕርዳር ዩኒቨርሲቲ መምህር እና ተመራማሪ ፕሮፌሰር ፈንቴ አምባው ኢትዮጵያ እና ኢትዮጵያውያን ለትምህርት ልዩ ትርጉም ሰጥተው መኖራቸውን አንስተዋል። የኢትዮጵያ የትምህርት ታሪክ ከሃይማኖት ተቋማት እንደሚጀመርም ገልጸዋል። ዘመናዊ የሚባለው ትምህርት ከአንድ ክፍለ ዘመን ብዙም ያራቀ ዕድሜ እንደሌለው ነው የተናገሩት። በሃይማኖት ተቋማት ሲሰጥ የኖረው ትምህርት እሴት ገንብቷል፣ ሀገርም አጽንቷል ይላሉ። በሃይማኖት ተቋማት የሚሰጠው ትምህርት ሥነ ምግባር ገንብቷል፣ መስረቅ፣ በሀሰት መመስከር፣ አለመታመን ነውር እንደኾነ ሲያስተምር ኖሯል።
ይህ ደግሞ ለማኅበረሰብ ግንባታ ትልቅ አስተዋጽኦ አለው ነው የሚሉት። ክፉ ነገር ማድረግ በሰዎች ዘንድ የሚያዋርድ እና በነፍስም ሀጥያት እንደኾነ እያስተማረ ትውልድ ቀርጿል ይላሉ። የዘመናዊ ትምህርትም የራሱን አስተዋጽኦ አድርጓል ያሉት ፕሮፌሰሩ ነገር ግን ውጤት ማምጣት የቻለ የዘመናዊ ትምህርት አለን ብለን መናገር አንችልም ነው ያሉት። “ትምህርት ላይ እሴት መጨመር ያስፈልጋል፤ የእኛ ማኅበረሰብም ለትምህርት ከፍተኛ ግምት የሚሰጥ በመኾኑ ዕሴት መጨመር ይገባል” ብለዋል።
አሁን ማንበብ እና መጽሐፍ መቻል ብቻ ዋጋ የለውም የሚሉት ፕሮፌሰሩ በዚህ ዘመን በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ የኾነ ትውልድ ያስፈልጋል፣ ማደግ ይቻላል የሚል ራዕይ ተይዞ እየተሠራ ከኾነ ተወዳዳሪ ትውልድ ማፍራት ላይ ቅድሚያ መስጠት ይገባል ነው ያሉት።
“በእኔ ዘመን ተማሪ ትምህርት ቤት የማይሄደው ብዙ የሚታረስ መሬት ስለነበር፣ ቤተሰብ ሥራ ስለሚበዛባቸው ነበር፤ አሁን ግን ተማሪዎች ወደ ትምህርት ቤት የማይሄዱት በግጭት እና በሌሎች ችግሮች ምክንያት ነው” ይላሉ።
የመማር ጽንሰ ሃሳብ እና ለትምህርት ሲሰጠው የነበረውን ዕይታ መቀየሩንም አንሱ። ቀደም ሲል ወላጆች በሥራ መብዛት ምክንያት ተማሪዎችን ወደ ትምህርት ቤት ለመላክ አይፈቅዱም ነበር፤ አሁን ግን መላክ ፈልገው እንዳይልኩ ኾነዋል አሉን። እያንዳንዱ ሰው ማኅበራዊ ግዴታ አለበት፤ ምሁራን ለትውልድ የሚጠቅመውን ነገር ማድረግ አለባቸው፤ ትምህርትን መደገፍ እና ለትምህርት መሥራት ማኀበራዊ እና ሞራላዊ ግዴታ ነው ያሉት። ምሁራን በቤታቸው ቁጭ ብለው ስለ ችግር መፍትሔ እያወሩ መኖር የለባቸውም። ወጥተው የመፍትሔ ሃሳባቸውን ማቅረብ አለባቸውም ብለዋል። በሚሊዮን የሚቆጠሩ ተማሪዎች ከትምህርት ገበታ ውጭ ኾነዋል ሲባል በቀላሉ ማየት እንደማይገባ ነው የተናገሩት።
ይህን ከባድ እና በትውልድ ላይ የከፋ ችግር የሚያመጣ መኾኑን መገንዘብ ይገባል ነው ያሉት።
በሚሊዮን የሚቆጠሩ ተማሪዎች ወደ ትምህርት ገበታ አልሄዱም ማለት ድህነት አጥቅቶናል፣ የትውልድ ልማት ላይም ወደኋላ ቀርተናል፣ ይሄን ማሰብ ግድ ይላል ብለዋል። የአማራ ክልል ሕዝብ ለሰው ሃብት ዕድገት ትልቅ ግምት ያለው ነው ያሉት ፕሮፌሰሩ በዚህ ጊዜ ያለውን እና የደረሰበትን ባሰብን ጊዜ ግን ስሜታዊ ያደርጋል ነው ያሉት። ትምህርት ላይ ካልሠራን የድህነት ምጣኔው ይጨምራል እንጂ መቀነስ አይቻልም ብለዋል። የተማሩ በቤታቸው ቁጭ ብለው በስልካቸው በፈጠሩት ግንኙነት አውሮፓ ላይ ተቀጥረዋል፤ ያልተማሩት ግን ለሥራ እያሉ በበረሃ ላይ እየሄዱ በዛው ተጎድተው እየቀሩሩ ነው፤ በውቅያኖስ ይሰጥማሉ። ትምህርት የዚህን ያክል ክፍተት ይፈጥራል ነው የሚሉት።
በትምህርት ጊዜ የሁለት ወራት ትምህርት መቋረጥ ለአንድ ዓመት ያክል የተማሩትን ዕውቀት ያስጠፋል የሚሉት ፕሮፌሰሩ ለሁለት ዓመታት ማቋረጥ ደግሞ አደጋው ከባድ ነው ብለዋል። ትምህርት ላይ ካልሠራን ችግሩ ውስብስብ ነው፤ ወደድንም ጠላንም ሀገርን ላልተማሩት ልጆች እናስረክባለን፤ ላልተማሩ ልጆች ሀገርን ካስረከብን ደግሞ ሀገር ልትሆን የምትችለውን ማሰብ ያስፈልጋል ነው ያሉት። ሀገር እንድትኖረን እና እንድታድግ እየፈለግን ለማን እንደምናስረክባት ማሰብ አለመቻል ግን ያሳምማል ይላሉ። እንደምንም ብለን በ2018 የትምህርት ዘመን ተማሪዎችን ወደ ትምህርት ቤት ካልመለስን አደጋው የከፋ ነው፤ ተማሪዎች በከፍተኛ የአዕምሮ ጫና ውስጥ ናቸው በማለት ገልጸዋል።
ያለ ትውልድ ግንባታ ሀገር ትርጉም አልባ ነው፤ ለሀገር የሚያስብ ሁሉ ትምህርት ቤቶችን መክፈት ይገባዋል፤ ትምህርት ቤቶችን ከግጭት ነጻ ማድረግ ግድ ይላል ነው ያሉት። ለትምህርት ዋጋ መክፈል ካለብን አሁን መክፈል አለብን ብለዋል። ምሁራን ከፍርሃት ቆፈን ወጥተው ዘመን ሳያልፍ ትምህርት ላይ መሥራት አለባቸው፤ ሀገርን ለተማረ ትውልድ ለማስረከብ ርብብር ያስፈልጋል፤ አሁን ሳይሠሩ ቆይተው ቢቆጩ ዋጋ የለውም፤ ጊዜው አሁን ነው ብለዋል። ከትምህርት መሪዎችም ቅንነት የተሞላበት ሥራ እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል። ለሕጻን ልጅ ብርጭቆ እንደማይሰጥ ሁሉ ሀገርን ላልተማረ እና ላልተዘጋጀ ሰው ላለመስጠት አሁን መሥራት ይገባል ነው ያሉት። ትምህርት ለአንድ ወገን ብቻ አይሰጥም፤ ሁሉም ትምህርት ላይ መሥራት አለበት ብለዋል። ሁሉም የማኅበረሰብ ክፍል ለትምህርት ድጋፍ ማድረግ እንዳለበትም ገልጸዋል።
ትምህርት እንዳይካሄድ የሚያድርግ የትኛውም አካሄድ ልክ አይደለም፤ ተማሪዎችን ጊዜው ሳያልፍ ማስመዝገብ ይገባል ነው ያሉት።
ዘጋቢ፦ ታርቆ ክንዴ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን