
ባሕርዳር: ነሐሴ 22/2017ዓ.ም (አሚኮ) መምህር አብርሃም መከተ ይባላሉ። ከ1967 ዓ.ም ጀምሮ በተለያዩ የመንግሥት ትምህርት ቤቶች 40 ዓመታትን፣ በግል ትምህርት ቤቶች ደግሞ 11 ዓመታትን አገልግለዋል።
በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች እንግሊዝኛ ቋንቋን አስተምረዋል። አሁን ላይ ደግሞ በባሕር ዳር ከተማ በሚገኘው አዞል አካዳሚ በማስተማር ሙያ ላይ ይገኛሉ። ትምህርት ከመጀመራቸው ከ1956ዓ.ም በፊት በልጅነት አለባበሱን በትኩረት የተመለከቱት መምህር ለሙያው ፍቅር እንዲያድርባቸው ማድረጉን ያስታውሳሉ። በ1964 ዓ.ም በደብረ ማርቆስ አጠቃላይ ሁለተኛ ደረጃ መምህራን ማሠልጠኛ የመምህርነት ሙያን አጥንተው በ1967 ዓ.ም ተመርቀዋል። በዚሁ ዓመትም የመምህርነት ሙያን እንደተቀላቀሉ ከአሚኮ ጋር በነበራቸው ቆይታ ገልጸዋል።
እርሳቸው ማስተማር በጀመሩበት ጊዜ ተማሪዎችን ለማብቃት ይሰጥ የነበረው ትምህርትም እጅ ሥራ፣ እርሻ፣ ጎጆ ኢንዱስትሪ እና ኑሮ በዘዴ እንደነበረም ነግረውናል። ጫካ ውስጥ በመግባት ቅጠል እየቀነጠሱ፣ አፈር እየቆፈሩ፣ ፊደላትን እየቀረጹ፣ ጭቃ ጠፍጥፈው የመገለገያ ቁሳቁሶችን በሸክላ እየሠሩ ሲያስተምሩ እንደነበረም ገልጸውልናል።
የመምህርነት ሙያም በወቅቱ እጅግ የተከበረ ሙያ እንደነበረ መምህር አብርሃም ያስታውሳሉ። ጥሩ ጊዜን በሙያው ላይ እንዳሳለፉም ነግረውናል። አሁን ላይ ያለው የመምህርነት ሙያ ክብር ከበፊቱ አንጻር ሲታይ ውስንነት እንዳለውም ትዝብታቸውን አጋርተውናል።
ከተማሪዎች ሥነ ምግባር አንጻር ላነሳንላቸው ሃሳብም እርሳቸው በሚያስተምሩበት ትምህርት ቤት ለመምህራን ክብር እና ፍቅር የሚሰጡ ምስጉን ተማሪዎች መኖራቸውን ጠቅሰዋል። በሌላ በኩል ደግሞ ወደ ጥቂት የመንግሥት ትምህርት ቤቶች ባቀኑባቸው አጋጣሚዎች መምህር ለመደባደብ ልብሳቸውን ከእጃቸው ከፍ ከፍ የሚያደርጉ እና ሌሎች የሥነ ምግባር ጥፋቶች ሲፈጥሩ የተመለከቷቸው አንገት የሚያስደፋ ጥቂት ተማሪዎች መመልከታቸውን አነሱልን። መምህራን ትምህርት ብቻ ሳይኾን ሥነ ምግባርም ነው የሚያስተምሩት፤ ለመጭው ትውልድ ተማሪዎችን የሚያበቁ፣ የሀገር ሃብት፣ ከተከበሩ እና ፍቅር ከተሰጣቸው ያላቸውን ነገር አሟጠው በማስተማር ልጆችን የሚያበቁ መኾናቸው መረሳት የለበትም ይላሉ።
አሁን ላይ ትምህርት ላይ ውጤት እንዲመጣ ጥረት የሚያደርጉ ተማሪዎች፣ መምህራን፣ ወላጆችና ሌሎች የሚመለከታቸው አካላት ቢኖሩም እየተመዘገበ ያለው ውጤት እንደሚጠበቀው እና እንደሚታሰበው እንዳልኾነ ገልጸዋል።
ትምህርት ቤት መምህሩን ነው የሚመስል ያሉት መምህር አብርሃም የትምህርት ጥራት ችግር ከመምህራን እና ከተማሪዎች ጥረት ውስንነት፣ ከብዙ ተማሪዎች የቤተሰብ ክትትል ውስንነት፣ ተምረው በአጥጋቢ ሁኔታ ሥራ ከማግኘት፣ ካለው ነባራዊ ሁኔታ አንጻር የተፈጠረ እንደኾነም የግል አስተያየታቸውን ጠቁመዋል። መፍትሄውም ሁሉም ባለ ድርሻ አካል የተለየ ጥረት እና ትግል ማደረግ ነው ብለዋል። መምህራን በመጀመሪያ የሚያስተምሩትን ትምህርት እና ሙያ ወደውትና አምነውበት ሊገቡ እንደሚገባ ገልጸዋል። ለትውልድ ከፍተኛ የኾነ መስዋዕትነት ሊከፍሉ እንደሚገባም አሳስበዋል። ባላቸው የሙያ ፍቅር በ2018 የትምህርት ዘመን የሚጠበቅባቸውን ተግባራት ለመከወን እና 52ኛ ዓመት የማስተማር ጊዜያቸውን ለመቀጠል ከወዲሁ ዝግጀት ላይ ናቸው።ያላቸውን ጉልበት አሟጠው በመጠቀም ለሌሎች መምህራን ትምህርት አስተላልፈው ለማጠናቀቅ ማሰባቸውንም በወኔ ገልጸውልናል። መምህራን በርትተው እንዲሠሩ እና ትውልዱን እንዲያበቁ የአደራ መልዕክታቸውንም አስተላልፈዋል።
ዘጋቢ:- ሮዛ የሻነህ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
