
ደሴ: ነሐሴ 23/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ከደቡብ ወሎ ዞን፣ ከሰሜን ወሎ ዞን፣ ከወልዲያ ከተማ፣ ከኦሮሞ ብሔረሰብ አሥተዳደር እና ከዋግኸምራ ብሔረሰብ አሥተዳደር የሰላም አማራጭን ለተቀበሉ የቀድሞ ታጣቂዎች የተሐድሶ ሥልጠና በኮምቦልቻ ከተማ መስጠት ተጀምሯል። በመርሐግብሩ ላይ የአማራ ክልል ምክትል ርእሰ መሥተዳድር አብዱ ሁሴን (ዶ.ር) እና የአማራ ክልል ሰላምና ጸጥታ ቢሮ ኀላፊ እሸቱ የሱፍ (ዶ.ር)ን ጨምሮ የፌዴራል እና የክልል ከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎች ተገኝተው ለሠልጣኞች አቀባበል አድርገውላቸዋል። የብሔራዊ ተሀድሶ ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር ብርጋዴር ጄኔራል ደርቤ መኩሪያ ኮሚሽኑ ወደ ሰላም የሚመጡ ታጣቂዎችን አወያይቶ ወደ መደበኛ ሕይወታቸው እንዲገቡ እያደረገ መኾኑን ጠቅሰዋል።
በአማራ ክልልም ጫካ ገብተው የነበሩ እና የሰላምን መንገድ የመረጡ የቀድሞ ታጣቂዎችን አመሥግነው ለሰላም ቅድሚያ መስጠታቸውን አድንቀዋል። ኮሚሽኑ በክልሉ በሦሥት የሥልጠና ማዕከላት ለቀድሞ ታጣቂዎች የተሃድሶ ሥልጠና እየተሰጠ መኾኑንም አንስተዋል። ኢትዮጵያን በጋራ ለማልማት እና ችግሮችን በመመካከር ለመፍታት ወጣቶች ትልቅ አደራ አለባችሁ ብለዋል። የአማራ ክልል ሰላም እና ጸጥታ ቢሮ ኀላፊ እሸቱ የሱፍ (ዶ.ር) “የሀገር ሽማግሌዎች እና የሃይማኖት አባቶች ያደረጉትን የሰላም ጥሪ ተቀብላችሁ ከትጥቅ ትግል ይልቅ ሰላማዊ አማራጭን መቀበላችሁ የሚያስመሠግን ነውም” ብለዋል። መንግሥት የሰላም አማራጭን የተቀበሉ ታጣቂዎችን በመደገፍ በልማቱ እንዲሳተፉ እንደሚያደርግም ጠቅሰዋል።
የአማራ ክልል ምክትል ርእሰ መሥተዳድር አብዱ ሁሴን (ዶ.ር) “የትናንትን ስህተት በነገ የሰላም ፍሬ ለመካስ በማሰብ የሰላም መንገድን ስለመረጣችሁ ደስተኞች ነን” ብለዋል። የኢትዮጵያ የወደፊት ተስፋ ወጣቶች በመኾናቸው ከጦርነት ይልቅ ሰላምን በማስቀደም ኢትዮጵያን ወደ ከፍታ መውሰድ እንደሚገባ አንስተዋል። አሁንም በጫካ የሚገኙ ወገኖች የችግር መፍቻ መንገዱ መመካከር በመኾኑ ሰላምን በመምረጥ ችግሮችን በንግግር መፍታት ይገባቸዋል ነው ያሉት። ክልሉ ዘላቂ የኾነ አሻጋሪ ዕቅድ በማዘጋጀት የጸጥታ ችግር እና ድህነትን መዋጋት ላይ ትኩረት አድርጎ ወደ ሥራ መግባቱን የጠቀሱት ምክትል ርእሰ መሥተዳድሩ የቀድሞ ታጣቂዎችም የበኩላቸውን እንዲወጡ አደራ ብለዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን