
ባሕር ዳር: ነሐሴ 23/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በአማራ ክልል “ሁሉን አቀፍ ልማት ያስመዘግባል” ተብሎ ተስፋ የተጣለበት የቀጣይ 25 ዓመት የአሻጋሪ እና ዘላቂ ልማት እቅድ ተዘጋጅቷል።
በዕቅዱ ላይ ከዚህ በፊት ለክልል የተለያዩ ባለድርሻ አካላት ሥልጠና ተሠጥቷ። አሁን ላይ ደግሞ ከነሐሴ 18/2017 ዓ.ም ጀምሮ ለዞን እና ለወረዳ የሥራ ኀላፊዎች ሥልጠናው እየተሠጠ ነው። በሥልጠናው ሲሳተፉ ያገኘናቸው የሁመራ ከተማ ምክትል ከንቲባ እና የንግድ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ በላይ ፈለቀ እንዳሉት ዕቅዱ ክልሉን ብሎም ሀገሪቱን ከድኅነት የሚያላቅቅ ነው። በምግብ ራስን ከመቻል ባለፈም ወደ ኢንዱስትሪ መር ምጣኔ ሃብታዊ እንቅስቃሴ ለመሸጋገር የተቀመጠውን ግብ የሚያሳካ መኾኑን ገልጸዋል። በ25 ዓመቱ ትኩረት ከተሰጠው ጉዳይ የንግድ ጉዳይ አንዱ መኾኑን ያነሱት ኀላፊው በቀጣይ ዓመታት ሕገ ወጥ ንግድን በመቆጣጠር የተረጋጋ የንግድ ሥርዓት መፍጠር አንዱ የትኩረት አቅጣጫ መኾኑን ገልጸዋል።
በቀጣይም የአካባቢውን ጸጋ በሙሉ አቅም በመጠቀም ክልሉ ለሚያስመዘግበው ልማት የድርሻቸውን ለመወጣት እንደሚሠሩ ነው የገለጹት።
ሌላኛው ተሳታፊ የደቡብ ወሎ ዞን መንገድ መምሪያ ኀላፊ ኢብራሂም ሀሰን እንዳሉት ዕቅዱ ክልሉ ያለውን ሃብት እና ሃብቱንም እንዴት ማልማት እንደሚገባ ያሳየ መኾኑን ገልጸዋል። ዕቅዱ የቀጣይ የሀገሪቱን ዕድገት የሚወስን እና የመካከለኛ ገቢ ባለቤት ኾኖ የማየት ራዕይ የያዘ መኾኑን ተናግረዋል፡፡ ክልሉን በመሠረተ ልማት በማስተሳሰር የተቀመጠውን ግብ የሚያሳካ፣ ከግብርና ወደ ኢንዱስትሪ የኢኮኖሚ ሽግግር የሚያፋጥን መኾኑንም ገልጸዋል።
የምዕራብ ጎጃም ዞን ሲቪል ሰርቪስ እና የሰው ሃብት ልማት መምሪያ ኀላፊ የሽሀረግ ታፈረ እንደገለጹት ዕቅዱ ከዚህ በፊት ያጋጠሙ ችግሮችን መውጫ መንገድ ያሳየ፣ በቀጣይ ደግሞ የመልካም አሥተዳደር፣ ምጣኔ ሃብታዊ እና ማኅበራዊ ልማትን በዘላቂነት የማረጋገጥ አቅም አለው።
የአማራ ክልል የፕላን እና ልማት ቢሮ የሕዝብ ግንኙነት እና ኮሙዩኒኬሽን ኀላፊ ሞገስ አያሌው ዕቅዱ ክልሉን በምጣኔ ሃብት፣ በማኅበራዊ እና በቴክኖሎጅ በዓለም ዓቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ የሚያደርግ ነው ብለዋል።
ዕቅዱን ለማሳካት ደግሞ በየደረጃው ለሚገኙ የሥራ ኀላፊዎች ሥልጠናዎችን መሥጠት እንዳስፈለገም አስገንዝበዋል። ከዚህ በፊት ለክልሉ ከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎች፣ ዳይሬክተሮች፣ ለሚዲያ ተቋማት እና ሌሎች የሚመለከታቸው አካላት ሥልጠናው ተሠጥቷል። በዚህ ዙር ደግሞ ለዞን፣ ለከተማ አሥተዳደር እና ለወረዳ የሥራ ኀላፊዎች ከነሐሴ 18/2017 ዓ.ም ጀምሮ እየተሠጠ ይገኛል። ሥልጠናው ነሐሴ 26/2017 ይጠናቀቃል። በቀጣይም ሥልጠናው ተጠናክሮ ይቀጥላል።
ዘጋቢ፦ ዳግማዊ ተሠራ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን