
ባሕር ዳር፡ ነሐሴ 23/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በአማራ ክልል ሁለንተናዊ ለውጥ ያመጣል ተብሎ የታመነበት አሻጋሪ የልማት እቅድ በማዘጋጀት ወደ ተግባር በመግባት ላይ ነው። ለተፈጻሚነቱም በየደረጃው ያለውን የፈጻሚና አስፈጻሚ አካላት በቂ ግንዛቤ በመፍጠር አቅም መገንባት አንዱ ስትራቴጂ ነው።
በአሻጋሪ እቅዱ ሥልጠና ሲሳተፉ ያገኘናቸው የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ምክትል ከንቲባ አስሜ ብርሌ አሻጋሪ የልማት እቅዱ የክልሉን ኢኮኖሚያዊ ሽግግር በሚገባ የሚያሳይ መሠረታዊ ግብ የያዘ ስለመኾኑ ይገልጻሉ። የከተማ እድገትን በማፋጠን ከተሜነትን ለማስፋፋት ታሳቢ ያደረገ ስለመኾኑም ጠቁመዋል። ከተሞች ለነዋሪዎች ምቹ ኾነው በፕላን እንዲመሩ የሚያስችል እቅድ መኾኑንም ነው ያነሱት። እቅዱ ከተሜነትን በሚያሳድግና የሥራ እድልን በሚቀንስ መንገድ የተዘጋጀ ኾኖ እንዳገኙት ተናግረዋል። በከተሞች አሁን ያለውን ከፍተኛ የሥራ አጥነት ችግር የሚፈታ እንደኾነም ነው የገለጹት።
በእቅዱ መሠረት መዋቅራዊ ሽግግሩ ሲተገበርና ኢኮኖሚው እያደገ ሲሄድ አምራች ኢንዱስትሪው እየተስፋፋና ሥራ አጥነትን ትርጉም ባለው ሁኔታ እንደሚቀንስም ነው ያመላከቱት። ለተግባራዊነቱም አልቆ መሥራት ያስፈልጋል ነው ያሉት። እቅዱን በሚገባ በፋጥነት መተግበርና ምርታማነትትን መጨመር ያስፈልጋል ነው ያሉት። ወደ ትግበራ በመግባትም ዕቅዱ ውጤታማ እንዲኾን ለመሥራት የሚያስችል ሥልጠና የወሰዱ ሰለመኾኑም ነው ምክትል ከንቲባው ያመላከቱት። የደቡብ ጎንደር ዞን የብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት የአደረጃጀት ዘርፍ ኀላፊ አምሳል ተስፋ አሻጋሪ እቅዱ በርካታ ጉዳዮችን የገለጠ መኾኑን ያነሳሉ። አይኾኑም እየተባሉ የቆዩት ጉዳዮችን ማድረግ እንደሚቻል ቀድሞ በግልጽ ያሳየ ነው ብለዋል።
የሌሎች ሀገራትን ተሞክሮ ከእኛ ሀገር ነባራዊ ሁኔታ ጋር ያዛመደ፣ ያለፉትን አፈጻጸማችንን በደንብ የተነተነ፣ የመሻገሪያ መንገዶችን ያሳየ ነው ብለዋል። ከዚህ በፊት የገጠሙንን ችግሮች የመውጫ መንገድ ያሳየ እቅድ እንደኾነም ነው የገለጹት። እቅዱ ቁጭትን ፈጥሮብናል የሚሉት ወይዘሮ አምሳል አጥተነው የነበረውን ሀብታችንን እና የመልማት ጸጋችንን በግልጽ እንድናየው አድርጎናል ነው ያሉት። ተቋማትን ከፋፍሎ በዘርፋ ያስቀመጠ ሚናውን የለየ በመኾኑ ተስፋን የሰነቀ እቅድ ስለመኾኑም አንስተዋል። የወሰዱትን ሥልጠና ተጠቅመው ከፈጻሚ አካላትና ከሕዝቡ ጋር ግልጽ ግንዛቤ በመፍጠር በቁጭት ለመሥራት መዘጋጀታቸውን ነው ያመላከቱት።
የሰሜን ወሎ ዞን ትምህርት መምሪያ ምክትል ኀላፊ ወንድወሰን አክሊሉ የልማት እቅዱ የክልሉን የመልማት አቅም በግልጽ ያሳየ መኾኑን ይገልጻሉ። በሁሉም ዘርፍ ያሉ አቅሞችንና ጸጋዎችን አውቆ በመፈጸም ሕዝቡን ተጠቃሚ ለማድረግ እድል የሚፈጥር መኾኑን አንስተዋል።
በየአካባቢው ያሉትን ሃብቶች በመለየትና በየደረጃው ያለው አመራር በጋራ ተግባብቶ ወደተግባር በመግባት ጥሩ ውጤት ማምጣት የሚያስችል ስለመኾኑም አመላክቷል።
ዘጋቢ፦ አሰፋ ልጥገበው
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!