የሳንባ ካንሰር እና መፍትሔዎቹ

9
ባሕር ዳር: ነሐሴ 23/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የዓለም ጤና ድርጅት መረጃ እንደሚያሳየው በገዳይነት ከሚታወቁ በሽታዎች መካከል የካንሰር በሽታ በቀዳሚነት የሚጠቀስ ነው። ከነዚያ ውስጥም የሳንባ ካንሰር አንዱ እና ዋነኛው እንደኾነ መረጃዎች ያሳያሉ።
የሳንባ ካንሰር ያልተለመደ የሕዋስ እድገት ከቁጥጥር ውጭ በኾነ መንገድ በሳንባ ውስጥ ሲከሰት የሚፈጠር በሽታ እንደኾነ የዘርፍ ባለሙያዎች ይናገራሉ፡፡ የሳንባ ካንሰር ከሳንባ ተነስቶ ወደ አንጎል እና ሌሎች የሰውነት ክፍሎች ሊሠራጭ የሚችል እንደኾነም እንዲሁ።ለሳንባ ካንሰር አጋላጭ ከኾኑ ምክንያቶች ውስጥ ደግሞ ትንባሆ ማጨስ እስከ 85 በመቶ የሚኾነውን ድርሻ እንደሚይዝ መረጃዎች ያሳያሉ። ይህም ጭሱ ውስጥ ብዙ መርዛማ ካንሰር አምጭ የኾኑ ኬሚካሎች ስላሉት እንደኾነም ነው መረጃው የሚያሳየው፡፡ በትንባሆ ከተጠቃሚው ባለፈ በተጠቃሚው ዙሪያ የሚገኙ ሰዎችም ጭምር ሊጎዱ ይችላሉ ይላል መረጃው፡፡ የአየር ብክለት፣ ምቹ ያልኾነ የሥራ ቦታ (በኬሚካል አካባቢ የሚሠሩ ሰዎች)፣ ውፍረት እና ብዙ አልኮል መውሰድ ለካንሰር በሽታ ሌሎች አጋላጭ ምክንያቶች ተደርገው በዓለም ጤና ድርጅት ድረ ገጽ ላይ ተቀምጠዋል።
ሳል፣ የደረት ሕመም፣ የአተነፋፈስ መቆራረጥ ወይንም የትንፋሽ ማጠር፣ ባልታወቀ ምክንያት የክብደት መቀነስ እና የምግብ ፍላጎት መቀነስ የበሽታው ዋና ዋና ምልክቶች እንደኾኑም መረጃው ያመለክታል፡፡
👉 የሳንባ ካንሰር እና ምርመራው
አካላዊ ምርመራ፣ ኢሜጂንግ (የደረት ራጅ፣ የኮምፒውተር ቶሞግራፊ ስካን እና ማግኔቲክ ሬዞናንስ ኢሜጂንግ)፣ ብሮንኮስኮፒን በመጠቀም የሳንባ ውስጠኛ ክፍልን መመርመር፣ የቲሹ (ባዮፕሲ) ናሙና በመውሰድ ምርመራ ማድረግ እንደሚቻልም መረጃዎች ያሳያሉ።
👉 የሳንባ ካንሰር እና ሕክምናው
የሳንባ ካንሰር ሕክምናዎች እንደ ካንሰሩ ዓይነት፣ እንደ በሽታው የሥርጭት መስፋፋት እና እንደ ሰውየው የሕክምና ታሪክ ይወሰናል። የሳንባ ካንሰርን ቀደም ብሎ ማወቁ ደግሞ የተሻሉ ሕክምናዎችን ለማድረግም ያግዛል ይላል። ቀዶ ጥገና፣ የጨረር ሕክምና፣ ኬሞቴራፒ፣ የታለመ ሕክምና (ታርጌትድ ቴራፒ) እና ኢሚውኖቴራፒ ከሕክምናዎች ውስጥ የሚጠቀሱ ናቸው።
👉 የሳንባ ካንሰር መከላከያ መንገዶች የሳንባ ካንሰር መከላከያ መንገዶች የመጀመሪያ እና ሁለተኛ ደረጃ የመከላከያ እርምጃዎችን የሚጠይቅ ነው። ትንባሆ አለማጨስ የሳንባ ካንሰርን ለመከላከል ዋነኛው እና የመጀመሪያው መንገድ እንደኾነም የዓለም ጤና ድርጅት መረጃ ያሳያል። የመጀመሪያ ደረጃ መከላከል ዋና ዓላማው ለበሽታው መከሰት መነሻ የኾኑ መንስኤዎችን መከላከል እና ጤናማ አካባቢን መፍጠር ነው። ከእነዚህ የመከላከያ እርምጃዎች ውስጥ ማጨስ ማቆም፣ ከጭስ ነጻ የኾኑ አካባቢዎችን መፍጠር፣ የትምባሆ ቁጥጥር ፖሊሲዎችን መተግበር፣ የሥራ አካባቢን ምቹ ማድረግ እና የአየር ብክለት መጠንን መቀነስ የሚሉት ይካተቱበታል። ስፖርት መሥራት፣ አመጋገብን ማስተካከል ማለትም ፍራፍሬ እና አትክልት አዘውትሮ መመገብ፣ የምግብ ፍላጎት መቀነስ፣ ድካም ስሜት ሲኖር እና ክብደት መቀነስ ሲከሰት ፈጥኖ መመርመር እንደሚያስፈልግም ይመከራል፡፡
ዘጋቢ፦ ዳግማዊ ተሠራ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
Previous articleየተማሪዎችን የሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ዕውቀት ከፍ የሚያደርግ ሥልጠና መስጠቱን የወልድያ ዩኒቨርሲቲ አስታወቀ።
Next articleአሻጋሪ የልማት እቅዱ ቁጭትን የፈጠረ ተስፋን የሰነቀ ዕቅድ ነው።