የተማሪዎችን የሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ዕውቀት ከፍ የሚያደርግ ሥልጠና መስጠቱን የወልድያ ዩኒቨርሲቲ አስታወቀ።

5
ወልድያ: ነሐሴ 23/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ወልድያ ዩኒቨርሲቲ ከሰሜን ወሎ ዞን፣ ከዋግኸምራ ብሔረሰብ አሥተዳደር እና ከወልድያ ከተማ አሥተዳደር ለተውጣጡ ለ150 የአንደኛ እና የሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎች ሥልጠና ሰጥቷል።
የወልዲያ ዩኒቨርሲቲ የአካዳሚክ ምርምር ቴክኖሎጂ ሽግግር እና ማኅበረሰብ አገልግሎት ምክትል ፕሬዝዳንት ማርዬ በለጠ (ዶ.ር) በሳይንስ ትምህርቶች ከፍተኛ ውጤት ያላቸው ተማሪዎች ተመርጠው ወደ ግቢ መግባታቸውን ገልጸዋል።ከ150 ተማሪዎች ውስጥ 30ዎቹ ቴክኖሎጂ የማበልፀቅ ዕቅድ ይዘው የገቡ እና በዩኒቨርሲቲው ድጋፍ የፈጠራ ሥራቸው ዕውን እንዲኾን የተደረጉ መኾናቸውን አብራርተዋል። 120 ተማሪዎች ደግሞ በ45 ቀን የዩኒቨርሲቲ ቆይታቸው የሳይንስ፣ የሂሳብ፣ የምህድስና፣ የቴክኖሎጂ እና የኢኖቬሽን ዕውቀታቸው ከፍ እንዲል መሠረት ተደርጎ ትምህርት መሰጠቱን ተናግረዋል።
በግቢ ቆይታቸው የተማሪዎቹ የሕክምና እና የትራንስፖርት ጨምሮ ሙሉ ወጭውን ዩኒቨርሲቲው መሸፈኑንም ገልጸዋል። ከሰሜን ወሎ ዞን ግዳን ወረዳ የመጣው ተማሪ መካሽ ደምሌ በራዳር ቴክኖሎጂ የማበልፀግ ፈጠራ ዕቅድ ይዞ ወደ ዩኒቨርሲቲው መግባቱን ነግሮናል። በግቢ ቆይታውም ለፈጠራ ሥራው አስፈላጊው ድጋፍ ተደርጎለት የፈጠራ ውጤቱን ለዕይታ አብቅቷል። ሌላኛው ከሰሜን ወሎ ዞን ጋዞ ወረዳ የመጣው ተማሪ አብርሃም ወዳጄ የእናቶችን ድካም ሊያቀል የሚችል የጤፍ ማበጠሪያ ማሽን ለመሥራት ያለውን ፍላጎት በዩኒቨርሲቲ ቆይታው የፈጠራ ሥራውን ዕውን ማድረጉን አስገንዝቧል። ተማሪዎቹ ቆይታቸውን አጠናቅቀው የፈጠራ ውጤታቸውን አሳይተዋል። ለሁሉም ተማሪዎች የደብተር እና እስክርቢቶ ድጋፍ መደረጉም ተመላክቷል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን

Previous articleመምህራን ተማሪዎች ተምረው ለቁም ነገር ሲደርሱ የሚሰማቸው ደስታ አንድ ገበሬ የዘራውን ሰብል ሲያጭድ የሚሰማው ስሜት ያክል ነው።
Next articleየሳንባ ካንሰር እና መፍትሔዎቹ