
ባሕር ዳር: ነሐሴ 23/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ትምህርት ላይ ያለውን ስብራት ለመጠገን ሁሉም እንዲተባበር የቀድሞ መምህራን ጠይቀዋል።
መምህራኑ ትምህርት ለግለሰብም ኾነ ለሀገር ዕድገት ወሳኝ መሠረት ነው ይላሉ። የዕውቀት እና የሙያ ሽግግር ሂደት የኾነውን ትምህርት ዛሬ ትተን ለነገ የምንለው ጉዳይ አለመኾኑንም አስረድተዋል። ከዚህ አኳያ ሁሉም የኅብረተሰብ ክፍል ለትምህርት ሥርዓቱ ስኬት በአንድነት መሥራት እንዳለበት የቀድሞ መምህራኑ ይናገራሉ። መምህር መልሳቸው መንግሥቱ ለ30 ዓመታት በመምህርነት ሲያገለግሉ ቆይተው ጡረታ ወጥተዋል። የመምህርነት ሞያ በቃል የሚገለጽ ሳይኾን በተማሪዎች ውጤት የሚታይ መኾኑን ይገልጻሉ። ተማሪዎች ተምረው ለቁም ነገር ሲደርሱ የሚሰማቸውን ደስታ “አንድ ገበሬ የዘራውን ሰብል ሲያጭድ ከሚሰማው ስሜት” ጋር አነጻጽረውታል። ኾኖም በሀገሪቱ በተለይም በአማራ ክልል ባለው የሰላም ችግር ምክንያት በትምህርት ላይ የደረሰው ተጽዕኖ በእጅጉ እንደሚያሳዝናቸው ተናግረዋል።
እንደ መምህር መልሳቸው መንግሥቱ ገለጻ የትምህርት መስተጓጎል የትውልድ ክፍተት እየፈጠረ ሲኾን ይህም ሀገር ከዓለም ጋር እንዳትወዳደር እንቅፋት ኾኖባታል ነው የሚሉት። ወላጆች ለልጆቻቸው የትምህርትን ዓላማ እና ጥቅም በማስረዳት ወደ ትምህርት ቤት እንዲመለሱ ማበረታታት ይገባቸዋል ብለዋል። መምህራን ተማሪዎችን በሥነ ምግባር በማነጽ ለኅብረተሰቡ ሞዴል እንዲኾኑ ማገዝ እንደሚገባቸውም ነው የጠቆሙት። መንግሥት ደግሞ ትምህርት ቤቶችን በማደስ እና አስፈላጊ ቁሳቁሶችን በማሟላት ተማሪዎች ትምህርታቸውን እንዲቀጥሉ መርዳት አለበት ነው ያሉት። መምህር ገቢያነሽ አዳነ ለ28 ዓመታት የመምህርነት አገልግሎት ሰጥተው አሁን ላይ በጡረታ ነው የሚገኙት። አሁን ያለውን ሁኔታ ሲመለከቱ በጣም ማዘናቸውንም ገልጸዋል።
ሀገር ልትቀጥል የምትችለው በትምህርት እና በትምህርት ብቻ እንደኾነ ያስረዳሉ። በሚሊዮን የሚቆጠሩ ተማሪዎች ከትምህርት በመስተጓጎላቸው ምክንያት ለብዙ ችግሮች እየተጋለጡ መኾኑንም ገልጸዋል። በዚህ ምክንያትም ሴት ተማሪዎች ወደ ጎጅ ልማዳዊ ድርጊቶች እየተመለሱ መኾኑን ተናግረዋል። በርካታ ተማሪዎች ተስፋ በመቁረጥ ለስደት እና ለአስከፊ ሕይዎት እየተጋለጡ እንደሚገኙም ነው ያብራሩት። ሁለቱም የቀድሞ መምህራን ባለፉት ዓመታት የባከኑትን ጊዜ በማሰብ ሁሉም የኅብረተሰብ ክፍል በመተባበር የ2018 የትምህርት ዘመን ስኬታማ እንዲኾን ከአሁኑ መዘጋጀት እንደሚገባው አሳስበዋል።
ዘጋቢ፦ ሰመሃል ፍስሃ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!