በተንቀሳቃሽ ማዕከላት የተላላፊ ያልኾኑ በሽታዎች ምርመራ እየተሰጠ ነው።

12
ደባርቅ: ነሐሴ 22/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የሰሜን ጎንደር ዞን ጤና መምሪያ ከደባርቅ ከተማ አሥተዳደር ጤና ጽሕፈት ቤት እና ከተለያዩ አጋር ተቋማት ጋር በመተባበር በተንቀሳቃሽ ማዕከላት ተላላፊ ያልኾኑ በሽታዎች የምርመራ አገልግሎት እየሰጠ ይገኛል።
በምርመራ አገልግሎቱ ከ3 ሺህ 600 በላይ የማኅበረሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ ለማድረግ መታቀዱ ተገልጿል። ዘገባው እስከ ተጠናቀረበት ጊዜ ድረስ ከ2 ሺህ 200 በላይ የማኅበረሰብ ክፍሎችን ማስተናገድ ተችሏል ተብሏል። የዞኑ ጤና መምሪያ የበጎ ፈቃድ አሥተባባሪ ዘባሲል ወልዳይ ማኅበረሰቡ ተላላፊ ካልኾኑ በሽታዎች ራሱን እንዲጠብቅ የግንዛቤ ፈጠራ ሥራ እና የቅድመ ምርመራ አገልግሎት እየተሰጠ ነው ብለዋል። የቅድመ መከላከል ሥራ ተመራጭ በሽታን የመከላከያ ዘዴ በመኾኑ የቅድመ ምርመራ ሥራው ይሄን የሚያግዝ ነው ብለዋል።
የደባርቅ ከተማ አሥተዳደር ጤና ጽሕፈት ቤት ተወካይ ኀላፊ ጸዳል ፍቃዱ ተላላፊ ያልኾኑ በሽታዎች ምርመራ በተንቀሳቃሽ ማዕከል መሰጠቱ ማኅበረሰቡ ተመርምሮ ራሱን እንዲያውቅ እና የቅድመ ምርመራ ባሕሉን እንዲያሳድግ ዕድል እንደሚፈጥር ተናግረዋል። ምርመራው በሁለት ተንቀሳቃሽ ማዕከላት እየተሰጠ እንደሚገኝ እና የማኅበረሰቡን የጤና ምርመራ ተደራሽነት እንደሚያሻሽልም አብራርተዋል። በምርመራ ሂደቱ የማኅበረሰቡ ተሳትፎ እና ተጠቃሚነት ከፍተኛ እንደነበር የገለጹት ወይዘሮ ጸዳል በቀጣይም ከአጋር ድርጅቶች ጋር በመተባበር ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጸዋል።
የምርመራ ሂደቱ ዋና አሥተባባሪ ዮሐንስ ስንታየሁ የተቀናጀ የምርመራ እና የግንዛቤ ፈጠራ ሥራ እየተሠራ ነው ብለዋል። የደም ግፊት ልኬታ፣ የስኳር በሽታ ምርመራ፣ የማህጸን በር እና ጡት ካንሰር ምርመራ እና የኮቪድ 19 ክትባት አገልግሎት በዋናነት እየተሰጡ እንደሚገኝ ተናግረዋል። በምርመራ ሂደቱ 650 የሚኾኑ የተለያዩ በሽታዎች ምልክት ያሳዩ የማኅበረሰብ ክፍሎችን ለተሻለ ሕክምና ወደ ጤና ተቋም ማድረስ መቻሉን አንስተዋል። ተጠቃሚዎች በበኩላቸው ምርመራው ከማኅበረሰቡ የዕለት ተዕለት የሕይወት እንቅስቃሴ ጋር የተገናዘበ በመኾኑ ጠቀሜታው የጎላ ነው ብለዋል። በቀላሉ ቅድመ ምርመራውን በማካሄድ ራስን ማወቅ እና ለተሻለ ሕክምና መዘጋጀት እንደሚያስችልም አክለዋል። በቀጣይም ቅድመ ምርመራው ተደራሽነቱን በማሳደግ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ጠይቀዋል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
Previous articleሁሉም ተባብሮ ትምህርት ቤቶች እንዲከፈቱ የሃይማኖት አባቶች ጥሪ አቀረቡ።
Next articleየማዳበሪያ ፋብሪካ ለመገንባት የተደረሰው ስምምነት ኢትዮጵያ ማዳበሪያ ለማስገባት የምታወጣውን ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ የሚያስቀር ነው።