
ባሕር ዳር: ነሐሴ 22/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ትምህርት የሁሉም መሠረት ነው። የዓለም ሥልጣኔ መነሻው፣ የቴክኖሎጂ ምንጩ፣ የኀያላን ሀገራት ዋናው ጉልበት ከትምህርት የሚገኝ ዕውቀት ነው። የዕውቀት መገኛው ደግሞ ትምህርት ቤት ነው። የዜጎች መብትም ነው።
መልካም ትውልድ በትምህርት ይቀረጻል፤ የትውልድ ስነ ምግባር በትምህርት ይታነጻል። ትምህርት ቤቶች የዕውቀት ገበያ፣ የሰብዕና መገንቢያ፣ የአዕምሮ ማበልጸጊያ፣ የማኅበራዊ ሕይወት መሠረት ናቸው። የአንድ ወቅት የትምህርት መሥተጓጎል ከግለሰብ ጀምሮ እስከ ሀገር ድረስ በቀላሉ ሊመለስ የማይችል ኪሳራ እና ውድቀትን ያስከትላል። ባለፉት ዓመታት በአማራ ክልል በተከሰተው ግጭት በርካታ ትምህርት ቤቶች ተዘግተዋል፤ በብዙ አካባቢዎች ትምህርት ተቋርጧል፤ ተማሪዎች ከትምህርት ገበታቸው ተስተጓጉለዋል። የዚህ ውጤት ዛሬ ላይ በጉልህ የማይታይ ቢመስልም ነገ ላይ ከሚገመተው በላይ አሉታዊ ውጤትን ያስከትላል። የትውልድ ክፍተትን ይፈጥራል። ለቀጣዩ ትውልድም እዳን ያወርሳል።
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የባሕር ዳር ሀገረ ስብከት ዋና ፀሐፊ መልዓከ ብርሃን ፍስሐ ጥላሁን ያልተማረ ሕዝብ ራሱን ማሥተዳደርም ኾነ ሠርቶ መኖር ይከብደዋል ብለዋል። ባለፉት ዓመታት በግጭቱ ምክንያት ትምህርት በመሥተጓጎሉ ያለ እድሜ ጋብቻ እና አላስፈላጊ ስደት እየጨመረ መምጣቱን አንስተዋል። በርካታ አስከፊ ድርጊቶችም ተከስተዋል ነው ያሉት። ያቋረጡ ተማሪዎች በቀጣይ ወደ ትምህርት ገበታቸው መመለስ ይገባቸዋል ብለዋል። የትኛውም ጥያቄ ይኑር ትምህርትን የሚያስቆም አጀንዳ መኖር የለበትም ነው ያሉት። ትምህርት ገለልተኛ የኾነ ማኅበራዊ አገልግሎት የሚሰጥበት ተቋም በመኾኑ ትምህርት ቤቶችን ነጻ በማድረግ ማስቀጠል ይገባል ነው ያሉት።
ዘመኑ የትምህርት በመኾኑ ወላጆች፣ መምህራን፣ የሃይማኖት አባቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎች በመተባበር ትምህርት ቤቶች ተከፍተው ትምህርት እንዲቀጥል ማድረግ እንደሚገባም መክረዋል።
በአማራ ክልል የእስልምና ጉዳይ ከፍተኛ ምክር ቤት የትምህርት እና የዳዋ ዘርፍ ኀላፊ ሼኽ መሐመድ ኢብራሂም ልጆችን ማስተማር ትውልድን መታደግ ነው ብለዋል። የቀለም ትምህርት የሥልጣኔ ምንጭ መኾኑንም አንስተዋል። ባለፉት ዓመታት በተፈጠረው የሰላም እጦት ምክንያት በቀለም ትምህርት በኩል ከስረናል ብለዋል። ሰላም ቅድሚያ የሚሰጠው በመኾኑ መንግሥትም ይሁን የታጠቁ ኀይሎች ለሰላም ትኩረት ሰጥተው ትምህርት ቤቶች እንዲከፈቱ ማድረግ ይገባል ነው ያሉት። ትምህርት የአዕምሮ ምግብ ነው ያሉት ሼኽ መሐመድ ትምህርት ቆመ ማለት ምግብ ማቆም ማለት ነው ብለዋል። የሰው ልጅ ለመኖር ምግብ እንደሚያስፈልገው ሁሉ የተሻለ ሕይወት እንዲኖረውም የቀለም ትምህርት እንደሚያስፈልገው አስረድተዋል። በእስልምና ሃይማኖት የትምህርት ጉዳይ አንዱ አጀንዳ አድርገው እየሠሩ መመኾኑም አንስተዋል። የታጠቁ ኀይሎችም ኾነ የመንግሥት አካላት የአንድ ዓመት የትምህርት መቋረጥ የትውልድ ማጣት መኾኑን በመገንዘብ በልዩ ኹኔታ ትምህርት እንዲቀጥል መሥራት ያስፈልጋል ነው ያሉት።
በኢትዮጵያ የሰሜን ምዕራብ ወንጌላውያን አብያተ ክርስትያናት ኅብረት ዋና ጸሐፊ መጋቢ ገብሬ አሰፋ የልጅነት ጊዜ ወርቃማ የሕይወት ዘመን በመኾኑ ልጆች ይህንን ወርቃማ ጊዜአቸውን በትምህርት ማሳለፍ እንደሚኖርባቸው ገልጸዋል። ልጆች ከትምህርት ቤት ውጭ ሲያሳልፉ ላልተፈለገ እና አደገኛ ወደ ኾነ ልምምድ ይገባሉ ነው ያሉት። ይህም ማኅበራዊ ቀውስ የሚያመጣ እና ትውልድ ገዳይ መኾኑንም አብራርተዋል።
የትምህርት ጉዳይ የትውልድ ጉዳይ ነው ያሉት መጋቢ ገብሬ በታሪክ ጥቁር ጠባሳ የሚጥል፣ ለጸጸት የሚዳርግ እንዳይኾን ባለድርሻ አካላት መረባረብ ይገባል ነው ያሉት።
መንግሥትም ይሁን የታጠቁ አካላት ቆም ብለው በማሰብ በክልሉ ትምህርትን ማስቀጠል እና ተማሪዎች ወደ ትምህርት ገበታቸው እንዲመለሱ ማድረግ እንደሚያስፈልግም አስገንዝበዋል። ሰላም የሁሉም መሠረት በመኾኑ በሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ሰላም እንዲመጣ እየተሠራ መኾኑንም የሃይማኖት አባቶች አንስተዋል። ሰላም ከሁሉም ይቀድማል፤ ሰላም ይውረድ ነው ያሉት። ሁሉም ተባብሮ ትምህርት ቤቶችም እንዲከፈቱ፣ ልጆችም ወደ ትምህርት ገበታቸው እንዲመለሱ የሃይማኖት አባቶች ጥሪ አቅርበዋል።
ዘጋቢ: አሰፋ ልጥገበው
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!