
ደብረ ብርሃን፡ ነሐሴ 22/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የሰላም አማራጭን የተቀበሉ የቀድሞ ታጣቂዎች የተሃድሶ ሥልጠና በደብረ ብርሃን ከተማ መሠጠት ተጀምሯል።
በሥልጠና ማስጀመሪያው ላይ የተገኙት በምክትል ርእሰ መሥተዳድር ማዕረግ የከተማ ዘርፍ አስተባባሪ እና የከተማ እና መሠረተ ልማት ቢሮ ኀላፊ አሕመዲን መሐመድ (ዶ.ር ) የታጣቂዎች መመለስ በክልሉ በተደረገ ተደጋጋሚ ውይይት የመጣ ውጤት ነው ብለዋል። የትጥቅ ትግሉ ለሕዝብ ያስገኘው ጥቅም እንደሌለ እና እንደማይኖር በመረዳት አሁንም በጫካ ያሉ ወገኖች ሰላማዊ አማራጭን በመከተል ሕዝቡን የሚክስ ሥራ መሥራት ይገባቸዋል ነው ያሉት። መንግሥት በተደጋጋሚ ያደረገውን የሰላም ጥሪ ተቀብለው በመምጣታቸው ምስጋና አቅርበዋል።
በክልሉ ባለፉት ሁለት ዓመታት ውስጥ ሰብዓዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ማኅበራዊ ቀውሶች ተከስተዋል ብለዋል። የዚህ ሁሉ ገፈት ቀማሽ ሕዝቡ መኾኑንም ገልጸዋል። የተፈጠረውን ቁጭት ወደ ልማት መቀየር እንደሚያስፈልግም አመላክተዋል። በሚሊዮን የሚቆጠሩ ተማሪዎች ከትምህርት ገበታ ውጭ ኾነው መኖራቸውን ያስታወሱት ኀላፊው ይህ ደግሞ ሀገርን ወደ ኋላ የሚጎትት እና በትውልድ የዕውቀት ቅብብሎሽ ላይ ክፍተት የሚፈጥር ነው ብለዋል። ጽንፍ መያዝ ሀገር እና ሕዝብን የሚጎዳ፣ የሚያጎሳቁል እንጂ ወደ ከፍታ የሚወስድ አስተሳሰብ አይደለም ነው ያሉት።
የቀድሞ ታጣቂዎች በሚወስዱት ሥልጠና ራስን የመግዛት፣ የተበደለውን ሕዝብ በሥራ የመካስ፣ ክልሉን የመደገፍ፣ ሌሎችን ከስህተት የመመለስ እና ዘላቂ ሰላምን የማምጣት ኀላፊነት እንዳለባቸውም አመላክተዋል። የኢትዮጵያ ብሔራዊ ተሀድሶ ኮሚሽን በክልሉ ሰላም እንዲሰፍን ለሚሠራው ሥራም ምሥጋና አቅርበዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!