ፕላን ኢንተርናሽናል ኢትዮጵያ ለመተማ ወረዳ ትምህርት ጽሕፈት ቤት የትምህርት ቁሳቁስ ድጋፍ አደረገ። 

15

ገንዳ ውኃ፡ ነሐሴ 22/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ፕላን ኢንተርናሽናል ኢትዮጵያ የተባለ ግብረ ሰናይ ድርጅት ከ5 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት የትምህርት ቁሳቁስ በምዕራብ ጎንደር ዞን ለመተማ ወረዳ ትምህርት ጽሕፈት ቤት ድጋፍ አድርጓል።

የመተማ ወረዳ ትምህርት ጽሕፈት ቤት ኀላፊ በየነ አዳነ ፕላን ኢንተርናሽናል ላደረገው ትብብር እና ድጋፍ ምሥጋና አቅርበዋል።

የተደረገው ድጋፍ የትምህርት ቤቶችን የግብዓት ችግር የሚቀርፍ መኾኑን ገልጸዋል። ይህም አንዱ ለትምህርት ጥራት መሻሻል ግብዓት አይነተኛ ሚና እንዳለውም አመላክተዋል።

የተደረገው ድጋፍም የቁሳቁስ ችግር ባለባቸው ትምህርት ቤቶች እንደሚሰራጭ ተናግረዋል።

ይህም በቁሳቁስ እጥረት ምክንያት ተማሪዎች ትምህርታቸውን እንዳያቋርጡ ያደርጋል ብለዋል።

የትምህርትን ስብራት ለመጠገን ድጋፍ እንደሚያስፈልግ ያነሱት ኀላፊው በቀጣይም ሌሎች ተቋማት ይሄን መልካም ተግባር በማየት ድጋፍ እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል።

የፕላን ኢንተርናሽናል ኢትዮጵያ የሎጀስቲክስ እና አሥተዳደር የመተማ ቅርንጫፍ ኀላፊ ገስጥ ንጉሤ ድርጅቱ በኢትዮጵያ በተለያዩ አካባቢዎች በድርቅ እና በግጭት ለተጎዱ የማኅበረሰብ ክፍሎች ድጋፍ ሲያደርግ መቆየቱን አንስተዋል።

አሁንም ድርጅቱ ከ5 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት የትምህርት ቁሳቁስ ለመተማ ወረዳ ትምህርት ጽሕፈት ቤት ድጋፍ ማድረጉንም ገልጸዋል።

ይህም ድርጅቱ ሰው ተኮር ተግባራት ላይ እንደሚሠራ ያምላክታል ብለዋል። ድርጅቱ ተማሪዎች በሳይንስ እና በቴክኖሎጂ ብቁ እንዲኾኑ ድጋፉን አጠናክሮ እንደሚቀጥልም አስገንዝበዋል።

በመተማ ወረዳ የዲበኩሉ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ርእሰ መምህር ወርቅነህ ብርሌው እና በላስታ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ርእሰ መምህር ስመኘው ወረታው በአዲሱ የትምህርት ዘመን ማኅበረሰቡን ያሳተፈ የመማር ማስተማር ሂደቱን በማጠናከር ተማሪዎችን ወደ ትምህርት ገበታ ለመመለስ እየተሠራ ነው ብለዋል።

ትምህርት ቤቶች በርካታ ቁሳቁስ እንደሚያስፈልጋቸውም ገልጸዋል።

የተደረገው ድጋፍም የትምህርት ቤቶችን እና የተማሪዎችን ችግር የሚፈታ መኾኑንም አስገንዝበዋል።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየማዳበሪያ ማምረቻ ኮምፕሌክስ የድርሻ ስምምነት መፈረሙን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ( ዶ.ር) ገለጹ። 
Next articleመንግሥትን የሰላም ጥሪ የተቀበሉ የቀድሞው ታጣቂዎች በደብረ ብርሃን ከተማ የተሐድሶ ሥልጠና ጀመሩ።