የሸማቾች መብት እና የነጋዴዎች ግዴታ እስከምን ድረስ ነው?

11

ባሕር ዳር: ነሐሴ 22/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የንግድ ውድድር እና ሸማቾች ጥበቃ አዋጅ ቁጥር 813/2006 የሸማቹን እና የንግዱን ማኅበረሰብ መብት እና ግዴታዎች በሰፊው የሚያስቀምጥ አዋጅ ነው።

 

አዋጁ በዋናነት በግብይት ምክንያት በሸማቾች አካል፣ ጤና እና ንብረት ላይ ጉዳት እንዳይደርስ የሸማች መብቶችን ለመጠበቅ የወጣ በመኾኑ በነጋዴው ሊከበሩ የሚገቡ ዋና ዋና ጉዳዮች ትኩረት የሚሹ ኾነው ተቀምጠዋል፡፡

 

በዋናነትም በቂ እና ትክክለኛ መረጃን የማግኘት መብት፣ የአካል ደኅንነት መብት፣ መስተንግዶ የማግኘት መብት፣ የልማት መብት እና ካሳ የማግኘት መብት በሚል የተገለጹ ናቸው።

 

በአማራ ክልል ፍትሕ ቢሮ የኢኮኖሚ ወንጀል ጉዳዮች ዳይሬክተር ሙሉጌታ አሻግሬ አምራቾች፣ አስመጭዎቸ፣ አከፋፋዮች እና ቸርቻሪዎች ለገበያ ስለሚያቀርቧቸው የንግድ እቃዎች ወይም አገልግሎቶች የት? ከምን ? እና በማን? እንደተሠሩ የማሳወቅ ግደታዎችን አዋጁ አንዳስቀመጠ በሰጡን መረጃ ገልጸዋል።

 

ምርቶች ምንጫቸው ምን እንደኾነ፣ አጠቃቀማቸው እንዴት መምሰል እንዳለበት፣ ዋጋቸው ስንት እንደኾነ፣ ስለአያያዝ እና አስተሻሸጋቸው ጭምር ትክክለኛ እና በቂ መረጃን ለሸማቾች እንዲሰጡ የሚያስገድድ እና የዚህ አይነቱን የገበያ ጉድለት የሚሞላ የሕግ ሥርዓት በአዋጁ በጥንቃቄ የሚታዩ ጉዳዮች እንደኾኑም አመላክተዋል።

 

የኢፌዴሪ የወንጀል ሕግም በአንቀጽ 527 ሥር አንድ ሰው ኾን ብሎ ለሰው ምግብነት የሚያገለግሉ ነገሮችን ወይም እቃዎችን የሕዝብ ጤናን በሚጎዳ ሁኔታ ያረከሰ ወይም ጎጅ የኾኑ የምርት ውጤቶችን ኾን ብሎ ለሽያጭ ያቀረበ፣ ያከማቸ፣ ወደ ውጭ የላከ፣ ወደ ሀገር ውስጥ ያስገባ፣ የተቀበለ፣ ያከፋፈለ ወይም ያከማቸ እንደኾነ ከስድስት ወር በማያንስ ቀላል እስራት የሚያስቀጣ እንደኾነ ያትታል።

 

ነገሩ ከባድ ሲኾንም ከአምስት ዓመት በማያንስ ጽኑ እስራት እና በመቀጮ ሊቀጣ እንደሚችል፣ ድርጊቱ የተፈጸመው በቸልተኛነት እንደኾነ ደግሞ እስከ ስድስት ወር ቀላል እስራት ወይም በመቀጮ ሊቀጣ እንደሚችል በግልጽ ያስቀመጠ መኾኑን አዋጁን መነሻ አድርገው ጠቅሰዋል።

 

በንግድ ውድድር እና ሸማቾች ጥበቃ አዋጅ አንቀጽ 14 መሠረት ማንኛውም ሸማች መብት እንዳለውም አዋጁ ተንትኖ አቅርቧል። በዋናነትም:-

 

👉 ስለሚገዛው ዕቃ ወይም አገልግሎት ጥራት እና አይነት በቂ እና ትክክለኛ መረጃ ወይም መግለጫ የማግኘት መብት

 

👉 ዕቃዎችን እና አገልግሎቶችን አማርጦ የመግዛት መብት

 

👉 የዕቃዎችን ወይም አገልግሎቶችን ጥራት ወይም አማራጮችን በማየቱ ወይም የዋጋ ድርድር በማድረጉ ምክንያት እንዲገዛ ያለመገደድ

 

👉 ማንኛውም ነጋዴ በትሕትና እና በአክብሮት የማስተናገድ፣ በነጋዴው ከሚደርስበት የስድብ፣ የዛቻ፣ የማስፈራራት እና የስም ማጥፋት ተግባር የመጠበቅ መብትም እንዳለው ያትታል።

 

👉 የንግድ ዕቃዎችን ወይም አገልገሎቶችን በመግዛቱ ወይም በመጠቀሙ ምክንያት ለደረሰበት ጉዳት፣ የንግድ ዕቃዎቹን ወይም አገልግሎቶቹን ከማቅረብ ጋር ተያይዞ በአምራችነት፣ በአስመጭነት፣ በጅምላ ሻጭነት፣ በችርቻሮ ሻጭነት ወይም በሌላ ማንኛውም ሁኔታ በአቅርቦቱ የተሳተፉ ሰዎች በተናጠል ወይም በአንድነት ካሳ እንዲከፍሉት የመጠየቅ መብቶች ይኖሩታል ይላል አዋጁ፡፡

 

በአዋጁ አንቀጽ 22 መሠረት ለነጋዴዎች የተከለከሉ ተግባራትንም ተንትኖ አስቀምጧል።

 

እነዚህም:-

 

👉 የንግድ እቃዎች እና አገልግሎቶች ስላላቸው ጥራት፣ መጠን፣ ብዛት፣ ተቀባይነት፣ ምንጭ፣ ባሕሪ፣ ውሁድ ወይም ጥቅም የተሳሳተ መረጃ መስጠት የተከለከለ ተግባር ነው።

 

👉 የንግድ ዕቃዎችን ሞዴል፣ አዲስ የተሠሩ፣ የተለወጡ፣ እንደገና እንደ አዲስ የተሠሩ ወይም ያገለገሉ ስለመኾናቸው ወይም በአምራቹ እንዲሠበሠቡ የተባሉ ስለመኾናቸው በትክክል አለመግለጽ ያስጠይቃል።

 

👉 የሌላውን ነጋዴ የንግድ ዕቃዎች እና አገልግሎቶች በአሳሳች ሁኔታ መግለጽ ክልክል ነው።

 

👉 የንግድ ዕቃዎች እና አገልግሎቶችን በማስታወቂያ እንደተነገረላቸው አለመሸጥ፣ ወይም ማስታወቂያው የመጠን ውስንነት መኖሩን ካልገለጸ በስተቀር ለሸማቾች በሚፈልጉት ልክ አለመሸጥ ክልክል ነው።

 

👉 ስለ ዋጋ ቅናሽ አሳሳች ወይም ሐሰተኛ መረጃ ማስተላለፍ በአዋጁ ያስጠይቃል።

 

👉 ከንግድ ዕቃ ወይም ከአገልግሎት ሽያጭ ጋር የተያያዘ የተገባ የዋስትና ግዴታን አለመወጣት

 

👉 የንግድ ዕቃ የሚያስፈልገው ጥገና ወይም የሚተኩ ክፍሎቹ እንደማያስፈልጉት አድርጎ ማቅረብ

 

👉 ማንኛውም አገልግሎት የመስጠት ሥራን በንግድ ተግባሩ ከሚታወቀው ደረጃ በታች ወይም ባልተሟላ ሁኔታ መስጠት

 

👉 ለሰው ጤናና ደኅንነት አደገኛ የኾነ፣ ምንጩ ያልታወቀ፣ የጥራት ደረጃው የወረደ፣ የተመረዘ፣ የአገልግሎት ጊዜው ያለፈ፣ ወይም ከባዕድ ነገሮች ጋር የተደባለቀ የንግድ ዕቃን ለሽያጭ ማቅረብ ወይም መሸጥ በጥብቅ መከልከሉም አዋጁ ያስረዳል።

 

👉 በንግድ ዕቃ ወይም የአገልግሎት ግብይት ማንኛውም የማጭበርበር ወይም የማደናገር ተግባር መፈጸም በሕግ የሚያስጠይቅ ነው።

 

👉 የሸማቹን መብት ለመጠበቅ ካልኾነ በስተቀር የንግድ ዕቃን ወይም አገልግሎትን አልሸጥም ማለት እንደማይቻልም ይገልጻል።

 

👉 የደረጃዎች ማሕተም መጠቀም የሚያስፈልጋቸው የንግድ ዕቃዎችን ወይም አገልግሎቶችን ያለ ደረጃ ማሕተም ለሽያጭ ማቅረብ ወይም መሸጥ በጥብቅ መከልከሉን አዋጁ ያትታል።

 

👉 የንግድ ዕቃን ወይም አገልግሎትን በንግድ ዕቃው ላይ ወይም በንግድ መደብሩ ውስጥ ከተለጠፈው ዋጋ አስበልጦ መሸጥም ያስቀጣል ይላል።

 

👉 የንግድ ዕቃዎች የተሠሩበትን ሀገር አሳስቶ መግለጽ ክልክል ነው። እነዚህን እና ሌሎች ሕጎችን አስመልክቶ አዋጁ የተከለከሉ ጉዳዮችን አብራርቶ አስቀምጧል።

 

ማንኛውም ነጋዴ ግዴታዎችን በመተላለፍ በሚኒስቴሩ ማስታወቂያ እጥረት አለባቸው የተባሉ የንግድ እቃዎችን አከማችቶ፣ ደብቆ ወይም በሕገ ወጥ መንገድ እያጓጓዘ ከተገኘ የንግድ እቃው የሚወረስ ከመኾኑ በተጨማሪ ውሳኔው ከሚሰጥበት ዓመት በፊት የነበረን የመጨረሻ ዓመት ዓመታዊ የሽያጭ ገቢውን ከ5 እስከ 10 በመቶ የገንዘብ ቅጣት እና ከ1 እስከ 5 ዓመት በሚደርስ ጹኑ እስራት ሊቀጣ እንደሚችል በአዋጁ ተመላክቷል፡፡

 

በገበያ ላይ እጥረት እንዳለበት በሚኒስቴሩ ማስታወቂያ የተነገረለትን የንግድ እቃ ለግል ወይም ለቤተሰብ ፍጆታ ከሚውለው መጠን በላይ ለማንኛውም ነጋዴ ላልኾነ ሰው (ሸማች) ማስቀመጥ ወይም መደበቅ ክልክል እንደኾነም በአዋጁ ተተንትኗል።

 

በተጨማሪም በሚመለከተው አካል ከተፈቀደው የስርጭት መስመር ውጭ ማጓጓዝ ወይም እንዲጓጓዝ ማድረግም እንደማይቻል በአንቀጽ 24 ንዑስ አንቀጽ አራት ስር ተቀምጧል፡፡

 

ይህን ግዴታ ተላልፎ በገበያ ላይ እጥረት ያለበትን የንግድ እቃ አከማችቶ፣ ደብቆ ወይም በሕገ ወጥ መንገድ ሲያጓጉዝ የተገኘ ማንኛውም ሸማች በአዋጁ አንቀጽ 43 ንዑስ አንቀጽ ስድስት መሠረት በወንጀል ተከሶ ከብር 5 እስከ 50 ሺህ በሚደርስ የገንዘብ መቀጮ እና በቀላል እስራት ሊቀጣ እንደሚችልም ተደንግጓል።

 

ከዚህ ባለፈም አንድ ነጋዴም ይሁን ነጋዴ ያልኾነ ሰው በገበያ ላይ እጥረት እንዳለባቸው የተነገሩ የንግድ እቃዎችን በሚያከማች፣ በሚደብቅ ወይም በሕገ ወጥ መንገድ በሚያጓጉዝበት ጊዜ አብሮ የተሳተፈ አሸከርካሪም በወንጀል እንደሚጠየቅ ተጠቅሷል። ከብር 3 ሺህ አስከ 50 ሺህ በሚደርስ የገንዘብ መቀጮ ተቀጥቶ የንግድ እቃዎቹ የሚወረሱ እንደኾነም ተመላክቷል።

 

ዘጋቢ፦ ሰለሞን አንዳርጌ

 

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

👇👇👇

https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

 

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን

Previous articleሕጻናት ባልመረጡት እና ባልፈቀዱት ችግር ከትምህርት ገበታ ውጭ ሊኾኑ አይገባም።
Next articleየአርሶ አደሮችን ሕይወት እየቀየረ ያለው የፍራፍሬ ምርት፦