ሕጻናት ባልመረጡት እና ባልፈቀዱት ችግር ከትምህርት ገበታ ውጭ ሊኾኑ አይገባም።

23

ሕጻናት ባልመረጡት እና ባልፈቀዱት ችግር ከትምህርት ገበታ ውጭ ሊኾኑ አይገባም።

ባሕር ዳር: ነሐሴ 21/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ባለፉት ሁለት ዓመታት በተፈጠረው የጸጥታ ችግር ምክንያት የመማር ማስተማሩ ሥራ ፈተና በዝቶበት ቆይቷል።

የሰሜን ሸዋ ዞን ትምህርት መምሪያ ኀላፊ ጸጋየ እንግዳወርቅ ትምህርት ከሁሉም ተቋማት በበለጠ ሰላም የሚፈልግ ተቋም ነው ብለዋል።

ባለፉት ሁለት ዓመታት በመማር ማስተማሩ ላይ በተፈጠረው ጫና በርካታ ተማሪዎች ከትምህርት ገበታ ውጭ መኾናቸውን ገልጸዋል። ይህ ደግሞ ከፍተኛ የኾነ የማኅበራዊ ቀውስ አስከትሏል፤ በርካታ ተማሪዎችን ለስደት ዳርጓል፤ ከፍተኛ የኾነ የሥነ ልቦና ጉዳት አድርሷል ነው ያሉት፡፡

ሁለቱ ዓመታት በሕጻናት ሕይወት ላይ የተፈረደባቸው እንደነበሩም አንስተዋል።

ይህ አካሄድ ለክልሉ ሕዝብ እና ለቀጣዩ ትውልድ ጠቃሚ አይደለም ነው ያሉት፡፡ በቀጣይም የትምህርት ተቋማት ከማንኛውም የፖለቲካ ማሥፈጸሚያ አጀንዳነት ነጻ በማድረግ ትውልድን መገንባት ይኖርብናል ብለዋል፡፡

“ሕጻናት ባልመረጡት እና ባልፈቀዱት ችግር ከትምህርት ገበታ ውጭ ሊኾኑ አይገባም” ያሉት ኀላፊው ማንኛውም ለአማራ ሕዝብ ያገባኛል የሚል ሁሉ ተማሪዎች ወደ ትምህርት ገበታቸው እንዲመለሱ እና ያለስጋት እንዲማሩ መተባበር ይኖርበታል ነው ያሉት።

እንደ ዞን ያለፉትን ዓመታት ሊያካክስ የሚያስችል የ2018 የትምህርት ዘመን ዕቅድ በማቀድ ወደ ሥራ መግባታቸውን ገልጸዋል፡፡ ከ600 ሺህ በላይ ተማሪዎችን ለማስተማር ዝግጅት ተደርጓል ነው ያሉት።

ይህንን ለማሳካት ባለፉት ዓመታት ያልተማሩ ተማሪዎችን መልሶ ወደ ትምህርት ገበታቸው ማምጣት፣ የወደሙ ትምህርት ቤቶችን መልሶ የማቋቋም፣ የማደስ እና ግብዓቶችን የማሟላት ሥራ እየተከናወነ እንደኾነ ነው የገለጹት፡፡

ተማሪዎች ወደ ትምህርት ገበታቸው እንዲመለሱ ማኅበረሰቡ እያገዘ መኾኑን የተናገሩት ኀላፊው ተማሪዎችም ለምን ትምህርት አንማርም የሚል ጥያቄ እያነሱ መኾናቸውንም አንስተዋል።

የሚመለከተው አካል ሁሉ የነበረውን የትምህርት ስብራት ለመጠገን የበኩሉን ድርሻ ሊወጣ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

ዘጋቢ:- ሰናይት በየነ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“ሕጻናት ላይ ካልሠራን ለትውልድ የሚተርፍ እዳ እንተዋለን” ዶክተር ከሰተብርሃን አድማሱ
Next articleየሸማቾች መብት እና የነጋዴዎች ግዴታ እስከምን ድረስ ነው?