
“ሕጻናት ላይ ካልሠራን ለትውልድ የሚተርፍ እዳ እንተዋለን” ዶክተር ከሰተብርሃን አድማሱ
ባሕር ዳር: ነሐሴ 21/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የሕጻናት አስተዳደግ ውጤታማ ሲኾን የትውልድ ግንባታው ስኬታማ ይኾናል። ሀገርም በትውልዶች ትጠቀማለች። ይህ ሳይኾን ሲቀር ግን የትውልድ ግንባታው የዘገየ እና ደካማ ይኾናል።
የቢግ ዊን ፊላንትሮፒ ድርጅት ዋና ሥራ አሥፈጻሚ ዶክተር ከሰተብርሃን አድማሱ የቀዳማይ ልጅነት ልማት የሕጻናት እንከብካቤ አስፈላጊ ነው፤ የሕጻንነት ዘመን የሰው ልጅ በፍጥነት የሚያድግበት እና የሚማርበት ወቅት ነው ይላሉ።
የሰው ልጅ አዕምሮ በ80 በመቶ የሚያድገው በመጀመሪያዎቹ 72 ወራት ውስጥ እንደኾነ አንስተዋል። በሕጻንነት ዘመኑ ትኩረት የተነፈገ፣ ተገቢ ተግባቦት ያልተፈጠረለት፣ ከወላጅ ወይም ከአሳዳጊ ጋር የመጫወት ዕድል ያላገኘ ከኾነ አዕምሮው አያድግም ነው የሚሉት።
የማያቋርጥ ጫና የአዕምሮን መዋቅር እንደሚቀየርም አንስተዋል።
“ሕጻናት ላይ ካልሠራን፣ ለትውልድ የሚተርፍ እዳ እንተዋለን” ነው ያሉት። ጨዋታ በሕጻንነት ዘመን ለአዕምሮ ዕድገት ቁልፍ ጉዳይ መኾኑንም ገልጸዋል።
ዕድገትን ለማረጋገጥ እና የተረጋጋ ኅብረተሰብ ለመገንባት የቀዳማይ ልጅነት እንከብካቤ እና ዕድገት ልማት፣ በተለይም ከልደት እስከ አምስት ዓመት መተግበር እጅግ መሠረታዊ ነው ይላሉ።
በዚህ ወሳኝ የዕድሜ ዘመን ላይ ትኩረት ካልሰጠን እና ሕጻናት ላይ ካልሠራን፣ በልጆች ላይ የአዕምሮ እድገት ውስንነት ይከሰታል፤ ይህ ደግሞ በተራው በጎልማሳነት ዘመን ሊኖረን የሚገባንን ብቃት ያቀጭጨዋል ብለዋል።
የተሟላ እንክብካቤ የተደረገለት ሕጻን የተሟላ አዕምሮ ይኖረዋል ያሉት ዶክተሩ በአስቸጋሪ ሁኔታ እና ቤተሰቡ ውስጥ ግጭት፣ ጭንቀት ባለበት ሁኔታ የሚያድግ ሕጻን ዕድገቱ ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ ያድርበታል ነው ያሉት።
ሕጻናት ነጻነት እና ሰላም ባለበት ቤት ውስጥ ሲያድጉ የአዕምሮ ዕድገታቸውም ላቅ ያለ መኾኑን ነው የተናገሩት። የበርካታ ወላጆች አስተዳደግ ልክ አይደለም የሚሉት ዶክተሩ ይህ ደግሞ በልጆች ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ ያሳድራል ነው ያሉት። ሕጻናት የመጀመሪያ ዓመት ላይ የሚሠሩ ሥራዎች በቀሪ ጊዜ ለሚታየው ውጤት አስተዋጽኦአቸው ከፍተኛ እንደኾነ ነው ያነሱት።
ሕጻናት የተሟላ ዕድገት እንዲኖራቸው ከተፈለገ ሲያለቅሱ ስልክ መስጠት አለያም እንዳያለቅሱ በሚል ምክንያት ሌሎች ቴክኖሎጂዎችን አሳልፎ መስጠት አይገባም ነው ያሉት።
በልጆች እና በአሳዳጊዎች መካከል የሚኖር መልካም ግንኙነት በልጆች የአዕምሮ ዕድገት ላይ አስተዋጽኦ እንዳለው ነው ያነሱት። በተለይም ከከተሜነት መስፋፋት ጋር ተያይዞ ልጆች አስተዳደጋቸው በአንድ ግቢ ውስጥ ብቻ እንዲኖሩ ይደረጋል፤ ይህ ደግሞ በልጆች አዕምሮዓዊ ዕድገት ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ አለው ነው የሚሉት።
የሕጻናት አስተዳደግ የተሟላ ካልኾነ በትምህርት ላይ ተወዳዳሪ አይኾኑም ብለዋል። በድህነት ውስጥ የሚወለዱ ሕጻናት ዕድገታቸው የተጎተተ እንደሚኾንም ገልጸዋል። ብዙ ሕጻናት በከፋ አስተዳደግ ውስጥ እንደሚያልፉም ተናግረዋል።
ለልጆች ተረት እና ታሪክ መንገር ብሎም መጻሕፍትን ማንበብ ለዕድገታቸው ትልቅ አስተዋጽኦ እንዳለው ነው የተናገሩት። ሕጻናትን በዚህ መንገድ ማሳደግ እሴትን ለማውረስ እንደሚያስችልም ገልጸዋል።
የአፍሪካ የቀዳማይ ልጅነት ልማት ማዕከል ምክትል ዋና ሥራ አሥፈጻሚ ዶክተር መሠረት ዘላለም የትውልድ ግንባታውን ውጤታማ ለማድረግ በቀደማይ ልጅነት ላይ ለውጥ ማምጣት ይገባል ነው ያሉት። በቀዳማይ ልጅነት ላይ ለውጥ ማምጣት ካልተቻለ ግን የትውልድ ግንባታው ልክ አይኾንም፤ ትውልድ እንዲፈጽማቸው የሚፈለጉ ዕቅዶችም የመሳካት ዕድላቸውን ይቀንሳል ብለዋል። የቀዳማዊ ልጅነት ልማትን ለማስፋት እየተሠራ መኾኑንም ገልጸዋል።
የቀዳማዊ ልጅነት ልማትን ውጤታማ ለማድረግ በቅድመ አንደኛ ትምህርት ቤቶች እና በሕጻናት ማቆያ መመገብ ያስፈልጋል ነው ያሉት። የሕጻናትን አዕምሮ ለማበልጸግ የሕጻናት ምገባ ቁልፍ ጉዳይ ነውም ብለዋል።
በአማራ ክልል ከቀደማይ ልጅነት ልማት ጋር በተያያዘ ጥናት ማድረጋቸውን የተናገሩት ዶክተር መሠረት በተደረገው ጥናት በርካታ ሕጻናት መድረስ በሚገባቸው የዕድገት ደረጃ እንዳልደረሱ ግኝት አለ ነው ያሉት።
“ከዓለም አቀፉ ልኬት አንጻር ሲተነተን በጣም ወደኋላ ቀርተናል” ብለዋል። የሕጻናት አዕምሮ ዕድገት እኛን ቆሞ አይጠብቅም ያሉት ዶክተር መሠረት በፍጥነት መሄድ ካልቻልን ተወዳዳሪ ትውልድ መፍጠር እንችልም ነው ያሉት።
ተወዳዳሪ ትውልድ ለመፍጠር መሠረቱ የቀዳማይ ልጅነት ልማት ነው ብለዋል። መሠረቱ ላይ ስላልሠራን ወደ ዩኒቨርሲቲ የሚገቡት ተማሪዎች ጥቂቶቹ ብቻ ናቸው ያሉት ዶክተር መሠረት ትውልዱን ተወዳዳሪ ለማድረግ መሠረቱ ላይ በትብብር መሥራት ይጠበቃል ብለዋል።
ዕድሜያቸው ለትምህርት የደረሱ ተማሪዎችም በብዛት ወደ ትምህርት ቤት እንደማይመጡ ነው የተናገሩት። የምግብ እጥረትም ለሕጻናት የአዕምሮ ዕድገት ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ አሳድሯል፤ መቀንጨርን እና መቀጨጭን ለማስቀረት በትኩረት መሥራት ይጠበቃል ነው ያሉት።
የሕጻናት ክትባት፣ የዕድገት እና የእናቶች እርግዝና ክትትል ለልጆች አዕምሯዊ ዕድገት ከፍ ያለ አስተዋጽኦ አላቸው ብለዋል።
የቀዳማይ ልጅነትን ውጤታማ ለማድረግ እናቶችን ማብቃት፣ ማንቃት እና የአንድ ሺህ ቀናት የሕጻናት እንክብካቤን በአግባቡ መፈጸም እንደሚያስፈልግም አመላክተዋል።
ዘጋቢ፦ ታርቆ ክንዴ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን